የሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና ከምድረ ገነት ሽሬ ጋር ጨዋታውን ያደርጋል - ኢዜአ አማርኛ
የሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና ከምድረ ገነት ሽሬ ጋር ጨዋታውን ያደርጋል
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 4 /2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 24ኛ ሳምንት ዛሬ ይጀመራል። በዕለቱ አራት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።
ምሽት 12 ሰዓት ላይ ሲዳማ ቡና ከምድረ ገነት ሽሬ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ሲዳማ ቡና በውድድር ዓመቱ ካከናወናቸው 23 ጨዋታዎች መካከል 11ዱን ሲያሸንፍ ሶስት ጊዜ ተሸንፏል። በቀሪ ዘጠኝ ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቷል። በጨዋታዎቹ ላይ 28 ግቦችን ሲያስቆጥር 14 ጎሎችን አስተናግዷል።
ቡድኑ በ42 ነጥብ ሊጉን እየመራ ነው።
በሊጉ ካደረጋቸው 24 ጨዋታዎች መካከል ስምንቱን ያሸነፈው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በበኩሉ አምስት ጊዜ ሽንፈት አስተናግዷል። በ10 ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል። 17 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 13 ግቦች ተቆጥረውበታል።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ34 ነጥብ አምስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ሲዳማ ቡና በ23ኛ ሳምንት በወላይታ ድቻ ካስተናገደው የ3 ለ 1 ሽንፈት በኋላ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታል። ድል ከቀናው ከተከታዩ ሃዋሳ ከተማ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ አምስት ነጥብ ከፍ ያደርጋል።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ ካሸነፈ ሶስተኛ ተከታታይ ድሉን ያስመዘግባል።
በሌላኛው መርሐ-ግብር ፋሲል ከነማ ከመቻል ከቀኑ 9 ሰዓት በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው።
ፋሲል ከነማ በሊጉ 23 ጨዋታዎችን በማድረግ ስምንት ጊዜ ሲያሸንፍ በአምስቱ ተሸንፏል። 10 ጊዜ ነጥብ ተጋርቷል። በጨዋታዎቹ ላይ 17 ግቦችን ሲያስቆጥር 15 ጎሎች ተቆጥረውበታል። ቡድኑ በ34 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
መቻል በውድድር ዓመቱ ካደረጋቸው 23 ጨዋታዎች በዘጠኙ ድል ሲቀናው ስድስት ጊዜ ተሸንፏል። በስምንት ጨዋታዎች አቻ ወጥቷል። 29 ግቦችን ከመረብ ጋር ሲያገናኝ 19 ጎሎች ተቆጥረውበታል። ቡድኑ በ35 ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
መቻል በዘንድሮው የውድድር ዓመት በርካታ ግቦችን ያስቆጠረ ክለብ ነው።
ፋሲል ከነማ ባለፉት ስድስት የሊግ ጨዋታዎች አላሸነፈም። መቻል በ23ኛ ሳምንት ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ጋር ያለ ግብ አቻ ተለያይቷል።
ሁለቱ ቡድኖች ወደ አሸናፊነት ለመመለስ የሚያደርጉት ጨዋታ ተመጣጣኝ ፉክክር ይደርግበታል ተብሎ ይጠበቃል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ ከባህርዳር ከተማ ምሽት 12 ሰዓት ላይ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።
የ16 ጊዜ የሊጉ አሸናፊ ቅዱስ ጊዮርጊስ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው በ25 ነጥብ 17ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። ቡድኑ ባለፉት ሰባት የሊግ ጨዋታዎች አላሸነፈም።
ባህር ዳር ከተማ በ28 ነጥብ 10ኛ ደረጃን ይዟል። ቡድኑ ባለፉት ሶስት ጨዋታዎች ከድል ርቋል።
ሁለቱም ቡድኖች ወደ አሸናፊነት መንገድ ለመመለስ ይጫወታሉ።
ሀዲያ ሆሳዕና ከሸገር ከተማ ከቀኑ 9 ሰዓት በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ሀዲያ ሆሳዕና በ29 ነጥብ ዘጠነኛ፣ ሸገር ከተማ በ27 ነጥብ 14ኛ ደረጃን ይዘዋል።
ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች አቻ የወጣው ሀዲያ ሆሳዕና ወደ ድል ለመመለስ ይጫወታል። ሸገር ከተማ ካሸነፈ ተከታታይ ድሉን ያስመዘግባል።
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 24ኛ ሳምንት እስከ መጋቢት 6 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል።
የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን የሲዳማ ቡናው አቤል ያለው እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንኩ አዲስ ግደይ በተመሳሳይ ዘጠኝ ግቦችን በማስቆጠር በጋራ እየመሩ ነው።
የፋሲል ከነማው ታምራት ኢያሱ በስምንት ግቦች ይከተላል።