የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች የሚሰጡት የሙያ ስልጠና የተጀመረውን ልማት ዳር ለማድረስ ያግዛል - ኢዜአ አማርኛ
የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች የሚሰጡት የሙያ ስልጠና የተጀመረውን ልማት ዳር ለማድረስ ያግዛል
ደብረ ማርቆስ ፤ መጋቢት 3/2018(ኢዜአ)፦በምስራቅ ጎጃም ዞን የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች የሚሰጡት በተግባር ላይ ያተኮረ የሙያ ስልጠና ሰላምን በማጽናት የተጀመረውን ልማት ዳር ለማድረስ የሚያግዝመሆኑን የዞኑ አስተዳደር ገለጸ፡፡
የምስራቅ ጎጃም ዞን አስተዳደር ''ለሰላም ዘብ እንቆማለን፣ የልማት አርበኛ እንሆናለን" በሚል ሀሳብ ከቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች መምህራንና ሰራተኞች ጋር የውይይት መድረክ ዛሬ በደብረ ማርቆስ ከተማ አካሄዷል።
የዞኑ ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ጌታሁን ፈንቴ በመድረኩ እንደገለፁት፤ መንግስት በየደረጃው የሚሰጠውን የትምህርት ጥራት በማረጋገጥ የአገሪቱን እድገት ቀጣይ ለማድረግ እየሰራ ይገኛል።
ለዚህም የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች የሚሰጡት በተግባር ላይ ያተኮረ የሙያ ስልጠና የተጀመረውን እድገት ዳር ለማድረስ መሰረት መሆኑን አስረድተዋል።
በዞኑ የተሳለጠ የመማር ማስተማር ስራ ለማከናወንም ቅድሚያ ለሰላምና ልማት መረጋገጥ በመትጋት ሊሆን እንደሚገባም አመልክተዋል።
የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ማህበረሰብ አባላትም በግንቦት ወር የሚካሄደው ምርጫ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ተዓማኒ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ግንባር ቀደም ሚና እንዲጫወቱም አሳስበዋል።
የዞኑ ቴክኒክና ሙያ መምሪያ ኃላፊ አቶ ጸሃይ ቦጋለ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች በመካከለኛ የሙያ ደረጃ የሰለጠነ የሰው ሃይል በማፍራት ኢኮኖሚውን እየደገፉ ይገኛሉ።
በየስልጠና ዘርፎቹ ብቁና ተወዳዳሪ፣ ስራ ፈጣሪና ለኢንዱስትሪ ልማቱ የጀርባ አጥንት የሆነ የሰው ሃይል በማፍራት አበረታች ውጤት ማስገኘታቸውን ገልጸዋል።
በተጨማሪም ከአካባቢ መስተዳድሮች ጋር በመተባበርም ወጣቶችን በአጫጭር የሙያና የገንዘብ አያያዝ ስልጠናዎችን በመስጠት ወደ ስራ እንዲገቡ እያገዙ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
ኮሌጆቹ ሲያደርጉት እንደነበረው አስተዋፅኦ ሁሉ ነጻና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለማካሄድ እየተደረገ ባለው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት እንዳለባቸውም አመልክተዋል።
በማቻከል ወረዳ የአማኑኤል ቴክኒክና ሙያ ምክትል ዲን አትጠገብ ደጀኔ ፤ ወጣቱን በአጫጭርና መካከለኛ ሙያ በማሰልጠን ስራ ፈጣሪ ለማድረግ ጠንክረው እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
የቴክኒክና ሙያ ስራ ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚችለው ሰላም ሲሰፍን መሆኑን አመልክተው በምርጫውም በንቃት ለመሳተፍ መዘጋጀታቸውን አረጋግጠዋል።
በመድረኩ ላይ በዞኑ ስር የሚገኙ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች አመራሮች፣ መምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞች ተሳትፈዋል።