በጋሞ ዞን ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች መልሶ ለማቋቋም መንግስት በተለየ ትኩረት ይሰራል - ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ - ኢዜአ አማርኛ
በጋሞ ዞን ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች መልሶ ለማቋቋም መንግስት በተለየ ትኩረት ይሰራል - ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ
አርባ ምንጭ፤ መጋቢት 3/2018(ኢዜአ)፦ በጋሞ ዞን ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች መልሶ ለማቋቋም መንግስት በተለየ ትኩረት እንደሚሰራ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ገለጹ።
ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር አለምፀሐይ ጳውሎስ፣ የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም(ዶ/ር) እና ሌሎች የፌዴራልና የክልሉ የስራ ሃላፊዎች በዞኑ በጋጮ ባባ ወረዳ ላካ ቀበሌ ተገኝተው ተጎጂዎችን አጽናንተዋል።
የካቲት 30 እና መጋቢት 1 ቀን 2018 ዓ.ም በአካባቢው በጣለው ከባድ ዝናብ ምክንያት በጋሞ ዞን ጋጮ ባባ እና ቦንኬ ወረዳዎች የመሬት መንሸራተት አደጋ ደርሶ በሰው ህይወትና በንብረት ላይ ጉዳት መድርሱ ይታወቃል።
በመሆኑም በአደጋው ሳቢያ ለተፈናቀሉ ወገኖች አስቸኳይ ሰብዓዊ ድጋፍና የመልሶ ማቋቋም ግብረ ሃይል ተቋቁሞ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑ ይታወቃል።
በአደጋው ስፍራ በመገኘት ተጎጂዎችን ያጽናኑት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ፤ ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች መልሶ ለማቋቋም መንግስት በተለየ ትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
በአሁኑ ወቅትም በክልሉ ዐቢይና ንዑሳን ኮሚቴዎች ተቋቁመው ወደ ተግባራዊ ስራ የገቡ መሆኑን ጠቁመው በአደጋው ለጉዳት የተዳረጉ ወገኖችን በዘላቂነት በማቋቋም ወደነበሩበት ህይወት እንዲመለሱ የክልሉ መንግስት አበክሮ ይሰራል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት በጎ ፈቃደኞች አስተባባሪ መላኩ መስፍን በበኩላቸው በትናንትናው እለት ለአስቸኳይ ጊዜ የሚሆን የተለያዩ ቁሶችን ለመጀመሪያ ዙር ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።
በዚህም በጋጮ ባባ ወረዳ የአልባሳትና ሌሎች አስፈላጊ ቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉን ጠቅሰው ድጋፉ የሚቀጥል ይሆናል ብለዋል።