በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለሀገር ይበጃል የምንለውን ፓርቲ ለመምረጥ ካርድ ወስደናል - ኢዜአ አማርኛ
በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለሀገር ይበጃል የምንለውን ፓርቲ ለመምረጥ ካርድ ወስደናል
ጊምቢ/ነገሌ፤ መጋቢት 3/2018(ኢዜአ)፦ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለሀገር ሰላምና እድገት ይበጃል የሚሉትን ፓርቲ መምረጥ የሚያስችላቸውን ካርድ መውሰዳቸውን በኦሮሚያ ክልል የምዕራብ ወለጋና የምስራቅ ቦረና ዞን ነዋሪዎች ገለጹ።
በምዕራብ ወለጋ ዞን የቤጊ ወረዳ ነዋሪ ወይዘሮ በቀሉ ቡልቶ ለኢዜአ እንደገለጹት ለልማትና ሰላም ቅድሚያ ሰጥቶ ለሚሰራ ፓርቲ ድምጽ መስጠት የሚያስችላቸውን የመራጭነት ካርድ መውሰዳቸውን ተናግረዋል።
ሌላው የወረዳው ነዋሪ ዳንኤል ዓለሙ በጠቅላላ ምርጫው መብቴን ያስጠብቅልኛል፣ ሀገርን ያሳድጋል ብዬ ያሰብኩትን ፓርቲ ለመምረጥ ከወዲሁ ካርድ ወስጃለሁ ብለዋል።
በተለይ የወጣቶችን የስራ አጥነት ችግር የሚፈታ፣ ለህብረሰተቡ ሁሉን አቀፍ የልማት ስራዎች ተደራሽ ማድረግ የሚያስችል አማራጭ ይዞ የሚቀርብ የፖለቲካ ፖርቲ ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን አመልክተዋል።
የጊምቢ ከተማ ነዋሪ ሳምሶን ቀጄላ በበኩላቸው ለሀገር ልማትና ሰላም ይበጃል የምለውን ፓርቲ ለመምረጥ ካርድ ወስጃለሁ ብለዋል።
በተመሳሳይ የምስራቅ ቦረና ዞን ነዋሪዎች በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ መምረጥ የሚያስችላቸውን የመራጭነት ካርድ መውስዳቸውን ተናግረዋል።
በዞኑ ሊበን ወረዳ የቡርሪ ቀበሌ ነዋሪ ታሪኩ አብዲ ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን በመጠቀም በሀገራዊ ምርጫው ለመሳተፍ የመራጭነት ካርድ መውሰዳቸውን ገልጸዋል።
የምርጫው ሂደት ሰላማዊ እንዲሆን የበኩላቸውን እየተወጡ እንደሚገኙም ተናግረዋል።
የነገሌ ቦረና ከተማ ነዋሪ ወጣት ማሙሽ ፈይሳም በምርጫው በመሳተፍ ዲሞክራሲያዊ መብቱን መጠቀም የሚያስችለውን ካርድ መውሰዱን ተናግሯል።