የመስኖ ልማት ስራው በአንድ ቦታ ተረጋግተን መኖር አስችሎናል - ኢዜአ አማርኛ
የመስኖ ልማት ስራው በአንድ ቦታ ተረጋግተን መኖር አስችሎናል
ጂንካ፤ መጋቢት 3/2018(ኢዜአ)፦ የመስኖ ልማት ስራው በአንድ ቦታ ተረጋግተው ማህበራዊ ኑሮ መመስረት እንዳስቻላቸው በደቡብ ኦሞ ዞን የዳሰነች ወረዳ አርብቶ አደሮች ገለፁ።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በደቡብ ኦሞ ዞን በቱርካና ሐይቅና በኦሞ ወንዝ ዳርቻ የሚገኙት የዳሰነች ወረዳ አርብቶ አደሮች በዋናነት በከብት እርባታ፣ በአነስተኛ ደረጃ ደግሞ በዓሳ ማስገርና በእርሻ ስራ ይተዳደራሉ።
በተለይም የኦሞ ወንዝ ሞልቶ ሲፈስ የሚተወውን እርጥበት ተጠቅመው ማሽላና በቆሎን በማምረት የሚታወቁ ሲሆን አሁን ላይ የመስኖ እርሻ ስራ ላይ በመሰማራት ተጠቃሚነታቸው በመጨመሩ ኑሯቸውን ተረጋግተው እየመሩ ይገኛሉ።
የወረዳው ነዋሪ አርብቶ አደር አረሚር ሎቾሪያ በመንግሥትና በአጋር ድርጅቶች ድጋፍ በመስኖ በቆሎ፣ ማሽላ፣ ማሾ እና የከብት መኖ እያመረቱ መሆኑን ገልፀው፥ የመስኖ ልማቱ የተረጋጋ ማህበራዊ ህይወት መመስረት እንዳስቻላቸው ተናግረዋል።
መንግሥት በደረቃማ አካባቢዎች እንድንሰፍር በማድረጉ ለጎርፍ ተጋላጭነታችን ቀንሷል ያሉት ደግሞ ሌላው የወረዳው ነዋሪ አርብቶ አደር ኦራር ናካሊ ናቸው።
ቀደም ሲል ለእንስሳት የግጦሽ ሳር ፍለጋና አልፎ አልፎ በሚከሰት የጎርፍ አደጋ የተረጋጋ ኑሮ እንዳልነበራቸው ገልፀው የመስኖ ልማት ከጀመሩ ወዲህ ግን በአንድ አካባቢ በመሆን የተረጋጋ ኑሮ መምራት መቻላቸውን ተናግረዋል።
በአካባቢው ትምህርት ቤቶች፣ የጤና ጣቢያዎችና ሌሎች ማህበራዊ ተቋማት በአቅራቢያ ስለሚገኙ አገልግሎቶችን በቅርበት እያገኙ መሆኑን ገልጸዋል።
ከእንስሳት እርባታው ጎን ለጎን የጀመረው የእርሻ ስራ የምግብ ዋስትናውን ከማረጋገጥ ባለፈ ተጨማሪ የገቢ ምንጭ እንዲያገኝ ማድረጉን የተናገረው ደግሞ ወጣት ሹመያ ለውሉል ነው።
ስለ እርሻ ስራ ምንም ዓይነት ዕውቀት እንዳልነበረው ጠቁሞ በግብርና ባለሙያዎች እገዛ በተፈጠረለት ግንዛቤ አሁን ላይ ቲማቲም፣ ሽንኩርትና ጥራጥሬዎችን በስብጥር እያመረተ መሆኑን ተናግሯል።
የእርሻ ስራው ከከብት እርባታው ጎን ለጎን የሚከወን በመሆኑ አዋጭ እንደሆነ ገልጾ ይህም በሌሎች ወጣቶች ዘንድ ተነሳሽነት መፍጠሩን ገልጿል።
የደቡብ ኦሞ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ ምንላርገው አዲሱ በበኩላቸው በቆላማ አካባቢዎች ከእንሰሳት እርባታው ጎን ለጎን የመስኖ ልማትን በማስፋፋት የአርብቶ አደሩን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
አርብቶ አደሩ ፈርጀ-ብዙ የገቢ አማራጭ ኖሮት በዘላቂነት ኑሮውን እንዲያሻሽል በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
በዞኑ በሚገኙ ስድስት አርብቶ አደር ወረዳዎች በበጋ መስኖ ከ10ሺህ ሄክታር በላይ መሬት እየለማ እንደሚገኝ ጠቁመው 26 ሺህ400 የሚሆኑ አርብቶ አደሮችም ተሳታፊና ተጠቃሚ መሆናቸውን አስረድተዋል።