ቀጥታ፡

ሴቶች ያላቸውን አቅምና እውቀት ለዘላቂ ሀገራዊ እድገት መጠናከር ሊያበረክቱ እንደሚገባ ተመላከተ

ሆሳዕና፤ መጋቢት 3/2018(ኢዜአ)፦ ሴቶች ያላቸውን አቅምና እውቀት ለዘላቂ ሀገራዊ እድገት መጠናከር ማበርከት እንደሚጠበቅባቸው የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር እናትዓለም መለሰ አመለከቱ።

"50 ዓመት የሴቶች ድምፅ ለእኩልነትና ለበለፀገች ኢትዮጵያ "በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀ ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ እየተከበረ ይገኛል፡፡


 

በወቅቱም የኢፌዴሪ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር እናትዓለም መለሰ እንዳሉት፤ ሴቶች ያላቸውን እምቅ አቅምና እውቀት ለዘላቂ ሀገራዊ እድገት መጠናከር ማበርከት ይጠበቅባቸዋል፡፡

ሴቶች ዛሬ ለደረሱበት የእኩል ተሳትፎና ተጠቃሚነት መረጋገጥ በርካት ትግል ስለመደረጉም አስታውሰዋል፡፡

ዛሬ እየተዘከረ በሚገኘው የግማሽ የክፍለ ዘመን ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ሴቶች ለሀገረ መንግሥት ግንባታው መጠናከር በተለያዩ ዘርፎች ከመሰማራት ባለፈ በትምህርት ዘርፍም የበኩላቸውን አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

እንዲሁም ሴቶች በጥናትና ምርምር፣ በምክንያታዊነት ላይ የተመሰረተና ኃላፊነቱን በአግባቡ ለመወጣት የሚችል ዜጋን በማፍራት ረገድም ትልቁን አስተዋፅኦ እያበረከቱ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡


 

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ ፋጤ ስርሞሎ በበኩላቸው በክልሉ የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የወጡ የህግ ማዕቀፎች ተግባራዊ እየተደረጉ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

በፖለቲካው፣ በኢኮኖሚና በማህበራዊ መስኮች ተሳትፏቸውን በማጠናከር እየተከናወነ በሚገኘው ስራ ተስፋ ሰጪ ውጤት እየተመዘገበ እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡

በከፍተኛ የትምህርት ተቋማትም የመማር ማስተማር ስራን ከማከናወን ባለፈ በሰላም ግንባታ፣ የሴቶች ተጋላጭነት መከላከልን መሰረት ያደረገ የጥናትና ምርምር ስራዎችን በማከናወን በኩል የሴት ምሁራን ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል።

የክልሉ ሴቶች ያላቸውን እውቀት በፖለቲካው ዘርፍም ለመጠቀም የተጀመረው ጥረት እንደሚጠናከር ነው የገለጹት፡፡


 

የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዳዊት ሀየሶ(ዶ/ር) እንደገለፁት በዩኒቨርሲቲው የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ጠቅሰው በመማር ማስተማር፣ በአመራር ሰጪነትና በሌሎች ኢኮኖሚያዊ መስኮች ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም