ቀጥታ፡

በዱር እንስሳትና ተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ የተከናወኑ ተግባራት ኢትዮጵያን ተወዳዳሪ የቱሪስት መዳረሻ ማድረግ አስችለዋል

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 3/2018(ኢዜአ)፦ በዱር እንስሳትና በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ዘርፍ የተከናወኑ ተግባራት ለኢኮ-ቱሪዝም ዕድገት ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ኢትዮጵያን ተወዳዳሪ የቱሪስት መዳረሻ ማድረጋቸውን የቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ።

የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን "60 ዓመታት ለኢትዮጵያ የዱር ሕይወት" በሚል መሪ ሀሳብ 60ኛ ዓመት የምስረታ በዓል የማስጀመሪያ መርሃ ግብር እያካሄደ ይገኛል።

በመርሃ ግብሩ የተገኙት የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ስለሺ ግርማ፤ ባለስልጣኑ ባለፉት ዓመታት የዱር እንስሳትን፣ የተፈጥሮ ሀብትንና ስነ-ምህዳርን ለመጠበቅ ሰፊ ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱን ገልጸዋል።


 

ኢትዮጵያ በብዝሃ የቱሪዝም ሀብት የታደለች መሆኗን የጠቀሱት ሚኒስትር ዴኤታው በጥበቃ ዘርፍ የተሰሩ ስራዎች ለኢኮ-ቱሪዝም አዳዲስ ዕድሎች መፍጠራቸውን ተናግረዋል።

ይህም የጎብኚዎችን ቁጥር በማሳደግ የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ለማጠናከርና ለዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን አብራርተዋል።

ይሁን እንጂ ዘርፉ አሁንም እንደ ህገ-ወጥ አደንና ንግድ እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥ ያሉ ተግዳሮቶች የጋራ ጥረት እንደሚፈልግ አሳስበዋል።


 

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ኩመራ ዋቅጅራ በበኩላቸው፤ ተቋሙ ባለፉት ስድስት አስርት ዓመታት ለብሔራዊ ፓርኮች መመስረት፣ ለተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና ህገ-ወጥ የዱር እንስሳት ንግድን ለመከላከል ውጤታማ ስራዎችን ማከናወኑን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት በመላ ሀገሪቱ በጥናት ላይ የተመሰረቱ 87 የጥበቃ ቦታዎች እንደሚገኙም አስታውቀዋል።

60ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ባለስልጣኑ ለኢትዮጵያ የዱር እንስሳትና ለመኖሪያ አካባቢያቸው ጥበቃ ያደረገውን ተቋማዊ አበርክቶ የሚዘክር ሲሆን፤ ከማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ባለፈ በሴሚናሮች፣ በአውደ-ርዕዮችና በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚከበር ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም