ፓርቲዎች በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም በሚያስጠብቁ አጀንዳዎች ላይ ሊያተኩሩ ይገባል - ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
ፓርቲዎች በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም በሚያስጠብቁ አጀንዳዎች ላይ ሊያተኩሩ ይገባል - ምሁራን
ሀዋሳ፤መጋቢት 3/2018 (ኢዜአ)፡-የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት የሀገርን አንድነት፣ ብሔራዊ ጥቅምና ልዕልናን በሚያስጠብቁ አጀንዳዎች ላይ ሊያተኩሩ እንደሚገባ ምሁራን ተናገሩ።
በመጪው ግንቦት 2018 ዓ.ም ለሚካሔደው 7ኛ ጠቅላላ ምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን እያከናወኑ ይገኛሉ።
ከዚህ ውስጥ አንዱ ፓርቲዎች በማኒፌስቷቸው መሰረት የያዟቸውን ዕቅዶችና ፖሊሲዎች ለመራጩ ህዝብ የማስተዋወቅና የሚያደርጓቸው ክርክሮች ይጠቀሳሉ።
ይህም ህዝቡ ለቀጣይ ይጠቅመኛል፤ ይወክለኛል ብሎ የሚያስበውንና የተሻለ ሀሳብ ያለውን የፖለቲካ ፓርቲ ለይቶ ለመምረጥ እንደሚያስችለው ይታመናል፡፡
በቅድመ ምርጫ ወቅት ፓርቲዎች እያደረጉት ያለውን ክርክር በተመለከተ ኢዜአ ያነጋገራቸው ምሁራን የፓርቲዎች ክርክር ሀገራዊ አንድነትና ብሔራዊ ጥቅምን በሚያስጠብቁ ጉዳዮች ላይ ማተኮር እንዳለበት ነው የገለጹት።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስነልሳን ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ባዬ ይማም እንዳሉት ምርጫ ህዝቡ ፍላጎቱን የሚገልጽበትና የዴሞክራሲ ስርዓት የሚጠናከርበት አንዱ መንገድ ነው፡፡
በመሆኑም ፓርቲዎች በቅድመ ምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ሀገርን አሸናፊ የሚያደርጉና ብሔራዊ ጥቅምን የሚያስጠብቁ ግልጽ ሀሳቦችን ማንሳት እንደሚገባቸው ነው የጠቀሱት፡፡
በተለይም ለሀገራዊ አንድነትና ደህንነት መከበር እንዲሁም ለሰላምና የህዝቦች ትስስር ቅድሚያ ሊሰጡ ይገባል ብለዋል፡፡
የሚቀርቡ የተለያዩ የፖለቲካ ዕሳቤዎች የህዝቦችን ትስስር ከማጠናከር ባለፈ የሀገርን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ልዕልና በሚያሳድጉ ወሳኝ ጉዳዮች ላይ ማተኮር እንዳለባቸው ጠቅሰዋል፡፡
ለሀገር ቀጣይነት ያለው ዕድገትና ለውጥ ምርጫ ወሳኝ መሆኑን ያነሱት ደግሞ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የስነልሳንና ስነተግባቦት መምህርና ተመራማሪ ፈቀደ ምኖታ (ዶ/ር) ናቸው፡፡
በምርጫ የሚወዳደሩ ፓርቲዎች የሚያቀርቡት ሀሳብ የህዝብን ኑሮ ከማሻሻልና ሀገራዊ ልማትን ከመደገፍ አንጻር በሚኖረው ጠቀሜታ ላይ ማተኮር እንዳለበትና ይህንንም ለህዝብ በግልጽ ማስረዳት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
በምርጫ ክርክር ወቅት ፓርቲዎች ግጭት ቀስቃሽ የሆኑ ቃላትና ንግግሮችን መጠቀም ተገቢ እንዳልሆነ አንስተዋል፡፡
በምርጫው ቢያሸንፉ መተግበር የሚችሉትን የፖሊሲ አማራጭና ጠቃሚ ጉዳዮች ላይ ቢያተኩሩ በህዝብ ዘንድ የተሻለ ተመራጭ ሊሆኑ እንደሚችሉ መክረዋል፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎች የሀገርን አንድነትና ልዕናን በሚያስከብሩ አጀንዳዎች ላይ ይበልጥ ማተኮር እንዳለባቸው የገለጹት ደግሞ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የእንግሊዝኛ ቋንቋና ስነፅሁፍ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ እንዳልካቸው ጀንበሬ (ዶ/ር) ናቸው።
በተለይ የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስጠብቁ ዕቅዶች ላይ የተሻለ ሀሳብ ይዘው በመቅረብ መከራከር እንዳለባቸው ገልጸው፣ አጀንዳዎቻቸውም የህዝቡንና የሀገርን ፍላጎት የተረዳ መሆን እንዳበት መክረዋል።
"የሀሳብ ልዩነት ቢኖርም ሀገር አንድ ናት" ያሉት እንዳልካቸው (ዶ/ር)፣ የትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ከሀገር ክብር አንጻር ዕቅድና ዓላማዎቹን ይዞ መቅረብ ይኖርበታል ብለዋል፡፡
የፓርቲዎች የምርጫ ክርክርና አቀራረብ ህዝብና ሀገርን የሚመጥን ሊሆን እንደሚገባ ጠቅሰው፣ ለዚህም በክርክሩ ወቅት ከቃላት አጠቃቀማቸው ጀምሮ ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባ አንስተዋል፡፡