የፋይዳ መታወቂያ ለወንጀል መከላከልና ምርመራ ስራዎች የላቀ ውጤታማነት አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የፋይዳ መታወቂያ ለወንጀል መከላከልና ምርመራ ስራዎች የላቀ ውጤታማነት አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 3/2018(ኢዜአ)፦ የፋይዳ መታወቂያ ለወንጀል መከላከልና ምርመራ ስራዎች የላቀ ውጤታማነት አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ገለጹ።
በፋይዳ መታወቂያ ዙሪያ ለፌደራል እና ክልል ፖሊስ አመራሮችና አባላት ግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ እየተካሄደ ነው።
ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ፋይዳ መታወቂያ ጸጥታ እና ደህንነት ለማስጠበቅ የሚሰሩ ስራዎችን ውጤታማ ለማድረግ ትልቅ ሚና አለው።
በተለይም የተለያዩ መታወቂያ እና ማንነትን በመጠቀም የሚፈጸሙ የወንጀል ድርጊቶችን በመከላከል በኩል ፋይዳው ከፍ ያለ መሆኑን ጠቅሰው፥ ውስብስብና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በመቆጣጠር ላይም ዓይነተኛ ሚና እንዳለው አብራርተዋል።
ህብረተሰቡን በማጭበርበር የወንጀል ድርጊቶችን የሚፈጽሙ አካላትን እንቅስቃሴ በመግታት በኩል ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አለው ብለዋል።
ስማርት ፖሊስ ስቴሽንን ጨምሮ ዘመናዊ የወንጀል መከላከል ስርዓት እየተዘረጋ መሆኑን ጠቁመው መሰል ስርዓቶችን ከፋይዳ ጋር በማስተሳሰር ለላቀ ውጤት እንደሚሰራ ተናግረዋል።
የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር ዮዳሄ አርዓያ ሥላሴ በበኩላቸው፤ ፋይዳ መታወቂያ የሰነድ ማጭበርበርን ለመከላከል አጋዥ መሆኑን አብራርተዋል።
ፋይዳ ከወረቀት ነጻ እና ቀልጣፋ አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለውም ነው የገለጹት።
ፋይዳ ለሕግ ማስከበርና ለወንጀል መከላከል ውጤታማነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቁመው የዲጂታል መታወቂያ ስርዓቱን ሙሉ በሙሉ ተደራሽ ለማድረግ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።