ቀጥታ፡

በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በዲጂታል የታገዘ የምርጫ ካርድ በመያዝ  ድምፃችንን ለመስጠት ተዘጋጅተናል

አሶሳ፤ መጋቢት 3/2018(ኢዜአ)፦ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በዲጂታል የታገዘ የምርጫ ካርድ በመያዝ  ድምፃቸውን ለመስጠት መዘጋጀታቸውን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የአሶሳ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።

በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ በወረቀት እና "ምርጫዬ" በተሰኘ መተግበሪያ በዲጂታል ዘዴ እየተከናወነ መሆኑ ይታወቃል።

ድምጻቸውን ለመስጠት የተመዘገቡ የአሶሳ ከተማ ነዋሪዎች እንደገለፁት፤ የመራጭነት ካርድ በዲጂታል አማራጭ መምጣቱ ዜጎች ባሉበት ሆነው ለመራጭነት የሚያበቃቸውን ካርድ እንዲይዙ ዕድል ፈጥሯል።

ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ አሳዲቅ ያሲን እንዳሉት፤ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የመራጮች ምዝገባ ዲጂታል አማራጭን ማካተቱ የወቅቱን የቴክኖሎጂ አስፈላጊነት ታሳቢ ያደረገ ነው ብለዋል።

በዲጂታል አማራጭ የመራጭነት ካርድ ማግኘት ቀላል በመሆኑ ዜጎች  በቀላሉ ለመመዝገብ ያስችላቸዋል ብለዋል።

ወይዘሮ ዙሁር ከማል እና አቶ እንዳለ አስራት በበኩላቸው፤ በምርጫው ለመሳተፍ የሚያስችላቸውን ካርድ በወቅቱ በመያዝ የድምፅ መስጫውን ቀን እየተጠባበቁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ነዋሪዎቹ በዲጂታል የያዙት የመራጭነት ካርድ ለዲጂታል ኢትዮጵያ የተሰጠው ትኩረት አንዱ ማሳያ መሆኑን ጠቁመው፥ መተግበሪያው የዜጎችን ጊዜ የሚቆጥብ እንደሆነ ተናግረዋል።

ህብረተሰቡ ለምርጫው የነቃ ተሳትፎ ማድረግ አለበት ያሉት ነዋሪዎቹ አሁን በያዙት ካርድ የነገ መሪያቸውን በመምረጥ ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን ሊጠቀሙ ይገባል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሁለት አይነት ያዘጋጀው የመራጮች ምዝገባ ዜጎች በፈለጉት አማራጭ የመራጭነት ካርድ እንዲይዙ የሚያደርግ በመሆኑ ዜጎች በምርጫው የነቃ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ያግዛል ያሉት ደግሞ ሌላዋ የወረዳው ነዋሪ ወይዘሮ ኬሪያ አብደላ ናቸው።

"በምርጫዬ" መተግበሪያ በቀላሉ የመራጭነት ካርድ መውሰዳቸውን ጠቅሰው ለመራጭነት የደረሱ ዜጎች ባሉበት ሆነው የምርጫ ካርድ መያዝ እንደሚችሉ ተናግረዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም