ኢትዮጵያ ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ያላትና ኢኮኖሚዋ እያደገ በመሆኑ የባህር በር ተዘግቶባት መኖር አትችልም - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ያላትና ኢኮኖሚዋ እያደገ በመሆኑ የባህር በር ተዘግቶባት መኖር አትችልም
ቦንጋ፤ መጋቢት 3/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ያላትና ኢኮኖሚዋ እያደገ በመሆኑ የባህር በር ተዘግቶባት መኖር እንደማትችል ምሁራን ገለጹ።
የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ተገቢ ምላሽ ማግኘት እንደሚገባውም ነው ኢዜአ ያነጋገራቸው ምሁራን የተናገሩት።
በቦንጋ ዩንቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ትምህርት ክፍል ያሬድ አያሌው(ዶ/ር)፣ ኢትዮጵያ ከባህር በር የተገለለችበትና እስካሁንም ተዘግታ የቆየችበት ጊዜ ከፍተኛ ቁጭት መፍጠሩን አንስተዋል።
በህግ፣ በታሪክም ሆነ በመልክአምድር አሁንም ሀገሪቱ ከቀይ ባህር የምትገለልበት አንዳችም ምክንያት የለም ሲሉም ነው የገለጹት።
በመሆኑም በአሁኑ ወቅት የባህር በር ጉዳይ የትውልዱ የህልውና ጥያቄ ሆኖ መምጣቱን አድንቀው በአፍሪካ ከፍተኛውን የህዝብ ቁጥር የያዘችው ኢትዮጵያ መግቢያና መውጫ ተዘግቶባት መኖር አትችልም ብለዋል።
በቦንጋ ትምህርት ኮሌጅ የጂኦግራፊና የአካባቢ ጥናት ትምህርት ክፍል መምህር አልማው ብሩ፤ ኢትዮጵያ ለቀይ ባህር የቅርብ እሩቅ ተደርጋ የኖረችበት ጊዜ የሚያስቆጭ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የራሷ የሆነ የባህር መውጫና መግቢያ ሊኖራት እንደሚገባና ይህንን የሚከለክል ምንም አይነት ምክንያት አለመኖሩን አንስተዋል።
የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ የትውልዱ ሚና ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።
በኮሌጁ የታሪክ መምህር እና ተመራማሪ ዘገዬ ወልዴማርያም(ዶ/ር)፤ የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤት መሆን ከራሷም አልፎ ለቀጣናው ሀገራት ትስስርና የጋራ ተጠቃሚነት የላቀ ትርጉም እንዳለው አስረድተዋል።
በኢትዮጵያ የትኛውም አይነት የፖለቲካ ለዩነት ቢኖር በሀገር ብሔራዊ ጥቅም ላይ ልዩነት ሊኖር እንደማይገባ አንስተው ክብሯንና ብሔራዊ ጥቅሟን ማስከበር የሁላችንም ሃላፊነት ነው ብለዋል።