በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ልማትና እድገት ያስቀጥላል የምንለውን ፓርቲ ለመምረጥ ካርድ ወስደናል-የአምቦ ከተማ ወጣቶች - ኢዜአ አማርኛ
በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ልማትና እድገት ያስቀጥላል የምንለውን ፓርቲ ለመምረጥ ካርድ ወስደናል-የአምቦ ከተማ ወጣቶች
አምቦ፤ መጋቢት 3/2018 (ኢዜአ)፡-በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ለመጀመሪያ ጊዜ በሚያደርጉት ተሳትፎ የአገር ልማትና እድገት ያስቀጥላል የሚሉትን ፓርቲ ለመምረጥ ካርድ መውሰዳቸውን የአምቦ ከተማ ወጣቶች ተናገሩ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት፣ ከየካቲት 28 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በየምርጫ ጣቢያዎቹ የመራጮች ምዝገባ እየተከናወነ ይገኛል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው በአምቦ ከተማ የሚገኙ ወጣቶች ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ፍትሃዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን ሚና ለመወጣት መዘጋጀታቸውንም ተናግረዋል።
ወጣቶቹ በምርጫው ንቁ ተሳትፎ በማድረግ፣ በሀገሪቱ የተጀመሩ የልማት ስራዎችን ያስቀጥላል ላሉት ፓርቲ ድምጻቸውን ለመስጠት መዘጋጀታቸውንም ገልጸዋል።
የከተማው ነዋሪ ወጣት ጌቱ ጉደታ ቀደም ሲል እድሜው ባለመድረሱ በምርጫ ተሳትፎ አድርጎ እንደማያውቅ ገልጿል።
አሁን መስፈርቱን አሟልቶ ለመጀመሪያ ጊዜ የመራጭነት ካርድ በመውሰዱ የተሰማውን ደስታ ገልጾ በምርጫው ለሀገር ይበጃል የሚለውን ፓርቲ ድምጹን ለመስጠት መዘጋጀቱን ገልጿል።
ሌሎች ወጣቶችም በጊዜ ሰሌዳ መሰረት የመራጭነት ካርድ መያዝ እንዳለባቸው መክሯል።
ሌላው ወጣት ሰለሞን ለማ ለመጀመሪያ ጊዜ የምርጫ ካርድ የወሰደው ለወጣቶች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትና ፖለቲካዊ ተሳትፎ ትኩረት የሚሰጥ ፓርቲ ለመምረጥ መሆኑን ተናግሯል።
''በተለይ በኢትዮጵያ የተጀመሩ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ቀጣይነት እንዲኖራቸው ይሰራል ብዬ ለማምነው ፓርቲ ድምፄን እሰጣለሁ" ሲል ገልጿል።
በዘንድሮው ምርጫ ሂደት ውስጥ በንቃት በመሳተፍ ለህዝብ እና ለሀገር ይጠቅማል የሚለውን ፓርቲ ለመምረጥ ካርድ ማውጣቱን የገለጸው ደግሞ ወጣት ቦና አበራ ነው።
7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ፣ ነጻ፣ ፍትሃዊና ተዓማኒ እንዲሆን ወጣቶች በራሳቸው ተነሳሽነት የሚጠበቅባቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱም ወጣቶቹ አስረድተዋል።
በአምቦ ከተማ የሆራ አይቱ ቀበሌ አካባቢ የሚገኝ ምርጫ ጣቢያ አስተባባሪ አቶ ግዛው ይልማ፤ ከየካቲት 28 ቀን ጀምሮ እየተከናወነ የሚገኘው የመራጮች ምዝገባ በተያዘለት እቅድ መሰረት እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
በጊዜ ሰሌዳው መሰረት በምርጫ ጣቢያው 1 ሺህ 500 ሰዎች ለመራጭነት ለመመዝገብ መታቀዱንም አንስተዋል።