በሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ሃዋሳ ከተማ ከድሬዳዋ ከተማ መቻል ከአርባምንጭ ከተማ የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ተጠባቂ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
በሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ሃዋሳ ከተማ ከድሬዳዋ ከተማ መቻል ከአርባምንጭ ከተማ የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ተጠባቂ ናቸው
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 3/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ 18ኛ ሳምንት ዛሬ ይጠናቀቃል።
ሃዋሳ ከተማ ከድሬዳዋ ከተማ ከረፋዱ አራት ሰዓት ላይ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ይጫወታሉ።
በሊጉ እስከ ካደረጋቸው 17 ጨዋታዎች መካከል 10ሩን ያሸነፈው ሃዋሳ ከተማ በሁለቱ ሽንፈት አስተናግዷል። በቀሪ አምስት ጨዋታዎች ላይ አቻ ተለያይቷል። በጨዋታዎቹ ላይ 31 ግቦችን ሲያስቆጥር 12 ጎሎችን አስተናግዷል።
ሃዋሳ ከተማ በ35 ነጥብ አራተኛ ደረጃን ይዟል።
ተጋጣሚው ድሬዳዋ ከተማ በውድድር ዓመቱ 17 ጨዋታዎችን አከናውኖ በስድስቱ ድል ሲቀናው 10 ጊዜ ተሸንፏል። በቀሪ አንድ ጨዋታ ነጥብ ተጋርቷል። 16 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 27 ጎሎች ተቆጥረውበታል።
ድሬዳዋ ከተማ በ19 ነጥብ ዘጠነኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
በ17ኛ ሳምንት ሃዋሳ ከተማ አዲስ አበባ ከተማን 3 ለ 1 አሸንፏል። ድሬዳዋ ከተማ በሊጉ መሪ ኢትዮ ኤሌክክትሪክ የ3 ለ 1 ሽንፈት አስተናግዷል።
ጨዋታው ሃዋሳ ከተማ በድል ጉዞው ለመቀጠል ድሬዳዋ ከተማ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ የሚያደርጉት ነው።
በሌላኛው መርሐ-ግብር መቻል ከአርባምንጭ ከተማ ከቀኑ 7 ሰዓት ላይ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
መቻል እስከ አሁን በሊጉ 17 ጨዋታዎችን ያደረገ ሲሆን 10 ጨዋታዎችን ሲያሸንፍ ሁለት ጊዜ ተሸንፏል። በአምስት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል።
በ17ቱ ጨዋታዎች ላይ 27 ጎሎችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 10 ግቦችን አስተናግዷል። ቡድኑ በ35 ነጥብ አምስተኛ ይዟል።
ተጋጣሚው አርባምንጭ ከተማ በበኩሉ ካከናወናቸው 17 ጨዋታዎች መካከል ሁለት ጊዜ ድል ሲቀናው በ11ዱ ተሸንፏል። በቀሪ አራት ጨዋታዎች ነጥብ ጥሏል። 10 ግቦችን ሲያስቆጥር 29 ጎሎች ተቆጥረውበታል።
አርባምንጭ ከተማ በ10 ነጥብ 13ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።
መቻል በ17ኛ ሳምንት ሲዳማ ቡናን 1 ለ 0 አሸንፏል። አርባምንጭ ከተማ ከአዳማ ከተማ ያለ ግብ አቻ ተለያይቷል።
ጨዋታው መቻል ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ፣ አርባምንጭ ከተማ ወደ ድል መንገድ ለመመለስ የሚያደርጉት ነው።
ሲዳማ ቡና ከባህርዳር ከተማ ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ሲዳማ ቡና በ21 ነጥብ ሰባተኛ ደረጃን ይዟል። ባህርዳር ከተማ በ10 12ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ሁለቱ ክለቦች በ17ኛ ሳምንት ካጋጠማቸው ሽንፈት በኋላ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይፋለማሉ።