ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደአክራ የሚያደርገው የቀጥታ በረራ የንግድ ትብብርን በማሳለጥ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ ነው-አምባሳደር ሮበርት አፍሪይ

አዲስ አበባ፤መጋቢት 2 /2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደጋና-አክራ የሚያደርገው የቀጥታ በረራ የሀገራቱን የንግድና የህዝብ ለህዝብ ትብብር በማሳለጥ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑን በኢትዮጵያ የጋና አምባሳደር ሮበርት አፍሪይ (ዶ/ር) ገለጹ።

አምባሳደር ሮበርት አፍሪይ(ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት፤ የኢትዮ-ጋና ግንኙነት በፓን አፍሪካኒዝም እሳቤ የተቃኘና ረጅም ዓመታትን ያስቆጠረ ነው።

የኢትዮጵያና ጋና ግንኙነትም በአጼ ኃይለስላሴ እና በፕሬዝዳንት ክዋሜ ንክሩማህ ዘመነ መንግስት በጽኑ መሰረት ታንፆ የቀጠለ መሆኑን ተናግረዋል።

በወቅቱም የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የአሁኑ የአፍሪካ ሕብረት እንዲመሰረት በማድረግ ብርቱ ተጋድሎ ማድረጋቸውን አንስተዋል።

በአሁኑ ወቅትም አፍሪካዊ ወንድማማችነትን በማጠናከር በመንግስታቱ ድርጅትና በአፍሪካ ሕብረት በሁለትዮሽና ባለብዙ ወገን ትብብር በጋራ እየሰሩ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

በሀገራቱ መካከል ያለውን የረጅም ዘመን ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነትም በንግድና ኢንቨስትመንት የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ የበለጠ ለማጠናከር በትኩረት እየሰሩ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የሀገራቱ የአየር ትራንስፖርት ትስስር በማጠናከሩም የንግድና ኢንቨስትመንት አጋርነትን ለማስፋት አስቻይ ሁኔታዎችን እየፈጠረ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

ለዚህም የአትዮጵያ አየር መንገድ ከአዲስ አበባ ወደ አክራ በቀን ከሶስት እስከ አራት የሚያደርጋቸው የቀጥታ በረራዎች የሀገራቱን ግንኙነት በማሳለጥ ትልቅ ዕድል እየፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህም የኢትዮጵያን የቆዳ ውጤቶች ምርቶችን ወደ ጋና በመላክና የጋናን የኮኮዋ ምርት ለኢትዮጵያ በማቅረብ ወሳኝ ዕድል መክፈቱን አስረድተዋል።

በአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነትም ለሀገራቱ የወጪና ገቢ ንግድ ትስስር መጠናከር ወሳኝ ሚና በመወጣት ለአህጉሪቷ ግቦች ስኬት መሠረት እንደሚሆን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም