የኃይማኖት ተቋማት በዜጎች መካከል አስተሳሳሪ ትርክት የሚያጠናክሩ አስተምህሮዎችን ማስፋት አለባቸው - ኢዜአ አማርኛ
የኃይማኖት ተቋማት በዜጎች መካከል አስተሳሳሪ ትርክት የሚያጠናክሩ አስተምህሮዎችን ማስፋት አለባቸው
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 2/2018 (ኢዜአ)፡-የኃይማኖት ተቋማት በዜጎች መካከል አስተሳሳሪ ትርክትን የሚያጠናክሩ አስተምህሮዎችን ማስፋት እንዳለባቸው በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ አብዱልቃድር ሬድዋን ገለጹ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሠላምና ጸጥታ ቢሮ ''የመደመር መንግሥት ለኃይማኖት ተቋማት ያለው ዕይታ'' በሚል መሪ ሃሳብ ከእስልምና ኃይማኖት አባቶች ጋር በተለያዩ ክፍለ ከተሞች ተወያይቷል።
ውይይት ከደረገባቸው ክፍለ ከተሞች መካከልም የአራዳ ክፍለ ከተማ አንዱ ሲሆን የኃይማኖት ተቋማት እስካሁን ያበረከቱት አስተዋጽኦ፣ የተገኙ ውጤቶችና ቀጣይ የቤት ሥራዎች ላይ ምክክር ተደርጓል።
በመድረኩም በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ አብዱልቃድር ሬድዋን፤ የኃይማኖት ተቋማት በሀገረ መንግሥት ግንባታና ትውልድ ቀረፃ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አላቸው ብለዋል።
የዘመናዊ ትምህርት ሥርዓት ባለነበረበት ወቅትም ትውልድን በሥነ-ምግባር በማነጽና የዜጎችን አብሮነት በማጎልበት የማይተካ ሚና ማበርከታቸውን ገልጸዋል።
በቀጣይም በዜጎች መካከል አስተሳሳሪ ትርክት ግንባታን ማጠናከር የሚያስችሉ አስተምህሮዎችን ማጠናከር እንደሚኖርባቸው አንስተዋል።
በአሁኑ ወቅትም በኃይማኖት ሽፋን በዜጎች መካከል ልዩነትን ለማስፋት የሚንቀሳቀሱ አንዳንድ ግለሰቦችን ከንቱ ፍላጎት ማክሸፍ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
በቀጣይም የኃይማኖት ተቋማት በሀገር ዘላቂ ሠላምና ልማት ግንባታ፣ በዜጎች አብሮነትና ትብብር መጎልበት በቁርጠኝነት ሊሰሩ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።
መንግስትም ከኃይማኖት ተቋማት ጋር የሚኖረውን ትብብር አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
የአራዳ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወንዱ ዑመር በበኩላቸው፤ የኃይማኖት ተቋማት በከተማዋና በሀገር ዕድገት ላይ ያላቸውን ወሳኝ ሚና አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋል።
በማህበራዊ ትስስር ገፆች ላይ የእምነትን ካባ በመልበስ የልዩነት መልዕክት የሚስተላልፉ ግለሰቦችንም መክሮና ገስፆ መመለስ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።
በመንግስት በኩል የኃይማኖት ተቋማት የሚያነሷቸውን ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ምላሽ እየሰጠ እንደሚሄድ አረጋግጠዋል።
ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል መሀመድ ሙሜ በሰጡት አስተያየት፤ የአዲስ አበባን ሰላምና ደኅንነት በማስጠበቅ ዕድገትን ለማስፋት ከመንግስት ጋር በቅርበት እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
ሌላው አስተያየት ሰጪ ሸምሱ ሙሰማ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያን ታሪካዊ ጠላቶች የጥፋት ህልም በማክሸፍ የሀገርን ዕድገት የሚያስቀጠል የተደመረ የትብብር አቅም ማጎልበት ይኖርብናል ብለዋል።
የኃይማኖት ተቋማትም የሀገርን ዕድገት በማስቀጠል የዜጎችን አብሮነት የሚያጎለብት አስተምህሮን ማስፋት እንደሚኖርባቸው አንስተዋል።
በማህበራዊ ሚዲያ ላይ በህዝቦች መካከል የልዩነት መልዕክቶችን የሚያስተላልፉ አካላት ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ ይገባል ያሉት ደግሞ ደግሞ ሌላው የውይይቱ ታሳተፊ መሀመድ ዑመር ናቸው።
መንግሥትም በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በኃይማኖቶች መካከል ጥርጣሬና አለመተማመን የሚፈጥሩ አካላት ላይ ተገቢውን እርምጃ ሊወስድ እንደሚገባ ገልጸዋል።