የዓለም አትሌቲክስ አህጉራዊ ውድድር መዳረሻ የሆነችው አዲስ አበባ - ኢዜአ አማርኛ
የዓለም አትሌቲክስ አህጉራዊ ውድድር መዳረሻ የሆነችው አዲስ አበባ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 2/2018 (ኢዜአ)፡- የዓለም አትሌቲክስ እ.አ.አ በ2026 አዳዲስ የኮንቲኔንታል ቱር ውድድሮች ይፋ ማድረጉ ይታወቃል።
ከነዚህ ውድድሮቹ አንዱ በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ የዓለም አትሌቲክስ አስታውቋል።
በመዲናዋ በሚገኘው የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ የሚካሄደው ውድድር በዓለም አትሌቲክስ የነሀስ ደረጃ እንደተሰጠው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የዓለም አትሌቲክስን ዋቢ በማድረግ ያወጣው መረጃ ያመለክታል።
ኢትዮጵያ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድር የማዘጋጀት እድል አግኝታለች።
የዓለም አትሌቲክስ ውድድሮቹን አስመልክቶ ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥቷል።
የአዲስ አበባ ግራንድ ፕሪ የዓለም አትሌቲክስ የነሀስ ደረጃ የተሰጠው ሲሆን ሚያዚያ 10/2018 ዓ.ም እንደሚካሄድ የወጣው መርሐ-ግብር ያመለክታል።
ኢትዮጵያ ፣ግብፅ ፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ሌሴቶ፣ ኦማን እና ሳዑዲ አረቢያ የዓለም አትሌቲክስ የ2026 አዳዲስ የኮንቲኔንታል ቱር ውድድሮች ከሚደረግባቸው ሀገራት መካከል ይጠቀሳሉ።
ውድድሩ ከተለያዩ ሀገራት የተውጣጡ አትሌቶች የሚሳተፉበት ከመሆኑ ባሻገር አሸናፊ የሚሆኑ አትሌቶች ከፍተኛ ሽልማት እንደሚያገኙ የዓለም አትሌቲክስ አስታውቋል።