ማህበሩ ከፍተኛ መጠን ያለው የቡና ምርት ለማእከላዊ ገበያ እያቀረበ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ማህበሩ ከፍተኛ መጠን ያለው የቡና ምርት ለማእከላዊ ገበያ እያቀረበ ነው
ዲላ፣መጋቢት 2/2018 (ኢዜአ)፦ከፍተኛ መጠን ያለው የቡና ምርት ለማእከላዊ ገበያ እያቀረበ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቡና አቅራቢዎች ማህበር አስታወቀ።
የማህበሩ ፕሬዝዳንት ዳንኤል ምጃኔ፤የቡና ምርትና ግብይቱ የማይቋረጥና ቀጣይነት ያለው በመሆኑ ለማእከላዊ ገበያ የማቅረቡ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ለኢዜአ ገልጸዋል።
የቡና ምርት ልማትና ግብይት ከንግድም ባለፈ ለሀገር የገቢ አቅም ማደግና ተጠቃሚነት ወሳኝ በመሆኑ በዚሁ መልኩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
በአንዳንድ አካባቢዎች የቡና ዋጋ ሊጨምር ይችላል በሚል የተሳሳተ ግምት የቡና ምርት ያከማቹ እንዳሉ አንስተው፥ እንዲህ አይነት ግምቶች ትክክል አለመሆናቸውንና ማንንም ተጠቃሚ አያደርጉም ሲሉ አስረድተዋል።
ከዚህም በመነሳት በክልሉ ከፍተኛ መጠን ያለው የቡና ምርት ለማዕከላዊ ገበያ እየቀረበ መሆኑን አንስተው ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል።
የጌዴኦ ዞን ቡና አቅራቢዎች ማህበር ሰብሳቢ ኢያሱ ወራሳ፤ በዞኑ የቡና ግብይቱ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቡናና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን ዋና ዳይሪክተር አቶ አማኑኤል ብሩ፤ በክልሉ በከፍተኛ ሁኔታ የቡና ምርት ለማዕከላዊ ገበያ እየቀረበ ስለመሆኑ ተናግረዋል።
በቀን በአማካይ ከ6 ሺህ 400 ኩንታል በላይ ቡና ወደ ማዕከላዊ ገበያ እየቀረበ መሆኑን ጠቁመው ወደፊትም በተጠናከረ መልኩ የሚቀጥል መሆኑን ገልጸዋል።
በክልሉ በተያዘው በጀት ዓመት ከ46 ሺህ 400 ቶን በላይ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ ታቅዶ እየተሰራ ሲሆን ባለፉት ሰባት ወራት ብቻ ከ19 ሺህ ቶን በላይ ማሳካት መቻሉን አስታውቀዋል።