ዓለም አቀፉ የቴሌኮሙኒኬሽን ሕብረት የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ስኬታማነት ድጋፍ ያደርጋል - ኢዜአ አማርኛ
ዓለም አቀፉ የቴሌኮሙኒኬሽን ሕብረት የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ስኬታማነት ድጋፍ ያደርጋል
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 2/2018 (ኢዜአ)፡- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ከዓለም አቀፉ የቴሌኮሙኒኬሽን ሕብረት (ITU) ዳይሬክተር ዶክተር ኮስማስ ዛቫዛቫ ጋር ዛሬ ተወያይተዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ኢትዮጵያ እና የቴሌኮሙኒኬሽን ሕብረቱ በዲጂታል ልማት ያለንን ትብብር ማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ቴሌኮምን ጨምሮ በዲጂታል መሠረተ ልማት ተደራሽነት፣ በዲጂታል ክህሎትና በተቋም ግንባታ እንዲሁም በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ትግበራ የተገኙ ተጨባጭ ውጤቶች አስደናቂ መሆናቸውን የሕብረቱ ዳይሬክተር እንደገለጹላቸው ተናግረዋል።
ይህንን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ ይበልጥ ለማፋጠን ከሕብረቱ ጋር ያለውን ትብብርም ወደ ላቀ ምዕራፍ ለማሸጋገር ውይይቱ አበርክቶው ላቅ ያለ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ በዘርፉ ያላትን የመሪነት ሚና ማሳደግና የሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ለዲጂታላይዜሽን፣ ዲጂታይዜሽንና ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን አጀንዳ ያለው ፋይዳ በተመለከተም ምክክር ማድረጋቸውንም ነው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹት።
የአቅም ግንባታ እና አዳዲስ የትብብር ዕድሎችን ማስፋት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይም መምከራቸውንም ጠቁመዋል።
በቀጣይም የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂን ከግብ ለማድረስ እና ትብብሩን ወደ ተሻለ ምዕራፍ ለማሸጋገር በተጀመሩ እና በሌሎች አዳዲስ ዘርፎች ዙሪያ በጋራ ለመስራት መስማማታቸውን አመልክተዋል።
በዘርፉ የሚደረጉ ዓለም ዓቀፍ ኮንፈረንሶችን በኢትዮጵያ በማዘጋጀት ሀገሪቷ ይበልጥ ስራዋን ለዓለም እንድትገልጥ በጋራ ለመስራት እንዲሁም ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ እንዲሳካ ለመደገፍና በዘርፉ ቀጣይነት ያለው ድጋፍ እንደሚቀጥል ከስምምነት ላይ መደረሱን ተናግረዋል።