ቀጥታ፡

የሲቪክ ማህበራት ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በስኬት እንዲጠናቀቅ ሚናቸውን ሊያጠናክሩ ይገባል

ደብረ ማርቆስ፤ መጋቢት 2/2018(ኢዜአ)፡-  በምስራቅ ጎጃም ዞን በመጪው ግንቦት ወር ለሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ ስኬታማነት የሲቪክ ማህበራት አስፈላጊውን እገዛና ድጋፍ በማድረግ ሚናቸውን ሊያጠናክሩ እንደሚገባ ተመላከተ።

‎"ለሰላም ዘብ እንቆማለን፣ የልማት አርበኛ እንሆናለን" በሚል ሀሳብ ከሲቪክ ማህበራት አደረጃጀቶች ጋር በደብረ ማርቆስ ከተማ የውይይት መድረክ ተካሄዷል።

‎የዞኑ ገንዘብ መምሪያ ኃላፊ አቶ አደመ መሰንበት በመድረኩ እንዳሉት፤ የሰላም እጦት ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴን የሚያዳክም ነው ብለዋል።

ስለሆነም የሲቪክ ማህበራት የተረጋጋ ሰላም እንዲሰፍን እና የህዝብ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ የልማት ተግባራት እንዲፋጠኑ የሚያደርጉትን አበርክቶ  አጠናክረው ማስቀጠል እንዳለባቸው ገልጸዋል።

ማህበራቱ በመጪው ግንቦት ወር የሚካሄደው ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ፣ ፍትሐዊና ተዓማኒነት ያተረፈ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሚናቸውን ሊያጠናክሩ ይገባል ብለዋል። 

የዞኑ ህብረት ስራ ማስፋፊያ ተጠሪ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ታረቀኝ ጀምበሬ በበኩላቸው፤ ሲቪክ ማህበራት በውስጣቸው ብዙዎችን ያቀፉና የሚያስተባብሩ በመሆናቸው ሰላምን ለመገንባት እና ልማትን ለማፋጠን ያላቸው ድርሻ የጎላ ነው። 

መንግስት ማህበራቱን እንዲያጠናክሩ እና ተጠቃሚ እንዲሆኑ በትኩረት እየሰራ ነው ያሉት አቶ ታረቀኝ ምርታማነታቸውን ለማሳደግም ቴክኖሎጂን በማቅረብ እና በማላመድ በኩል በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የተጀመሩ የልማት ስራዎችና የሰላም ግንባታን ዘላቂ ለማድረግም የውስጥ አንድነትን ማጠናከር የውጭ ተጋላጭነትና ስጋትን በመቀነስ በጋራ መስራት እንደሚገባ አንስተዋል። 

‎የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው በአካባቢው ዘላቂ ሰላም ለመገንባትና ልማትን ለማፋጠን እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን ከማገዝ ባሻገር ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በስኬት እንዲከናወን በቅንጅት እንሰራለን ብለዋል።

በመድረኩ የሴቶች፣ የወጣቶች፣ የመምህራን፣ የህብረት ስራ ማህበራት እንዲሁም መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና የተለያዩ የስራ ኃላፊዎችና ተወካዮች ተሳታፊ ሆነዋል።‎

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም