ቀጥታ፡

ምርጫው ዴሞክራሲያዊ፣ሰላማዊና ተዓማኒ እንዲሆን የድርሻችንን እንወጣለን

ወልዲያና ገንዳ ውሃ፤ መጋቢት 2/2018 (ኢዜአ)፦ሰላምን በማፅናት ጠቅላላ ምርጫው ዴሞክራሲያዊ፣ሰላማዊና ተዓማኒ እንዲሆን የድርሻችንን እንወጣለን ሲሉ የወልዲያና ገንዳ ውሃ ነዋሪዎች ተናገሩ።

የወልድያ ከተማ አስተዳደርና የምእራብ ጎንደር ዞን “ለሠላም ዘብ እንቆማለን፣ የልማት አርበኛ እንሆናለን " በሚል መሪ ሃሳብ ከእድር፣ ወጣትና ሴቶች አደረጃጀቶች እንዲሁም ከመምህራን ጋር ዛሬ ውይይት አካሂደዋል።

ነዋሪዎቹ በአካባቢያችን ሠላምን በማፅናት ምርጫው ዴሞክራሲያዊ፣ሰላማዊና ተዓማኒ ሆኖ እንዲከናወን የድርሻችንን እንወጣለን ብለዋል።

በወልዲያ ከተማ በተካሄደው ውይይት ላይ ከተሳተፉት መካከል አቶ መልካም ደምወዝ፣ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመፍታት የተጀመረውን ልማት ለማስቀጠል እንሰራለን ብለዋል።

በህግ ማስከበር ዘመቻው ያሳየነውን ድጋፍና የደጀንነት ሚና አሁንም አጠናክረን በማስቀጠል ለዘላቂ ሰላም መስፈን በጽናት እንቆማለን ነው ያሉት።

አሁን ያለውን ሠላም በማስቀጠል በዘንድሮው ምርጫ በንቃት ለመሳተፍ የጀመርነውን ስራ አጠናክረን እንቀጥላለን ያለችው ደግሞ ወጣት አበባ ሰማው ናት።


በምዕራብ ጎንደር ዞን በገንዳ ውሃ ከተማ በተካሄደው መድረክ ላይ የተሳተፉ መምህራን በበኩላቸው ትውልዱ የኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ታሪክ ተገንዝቦ የራሱን ታሪክ ለመስራት እንዲነሳሳ እንሰራለን ሲሉ ተናግረዋል።

ከተሳታፊዎቹ መካከል መምህር አበበ ምንተስኖት እንዳሉት፤ እኛ መምህራን ትውልዱን በመልካም እሴትና በሀገር ፍቅር ስሜት መቅረፅ ይኖርብናል ብለዋል።

የጋራ ትርክትን ማስረጽ ላይ በማተኮር ሀገሪቱን እየፈተኗት የሚገኙትን የመጠራጠር፣ የመከፋፈልና የግለኝነት እሳቤዎችን በማስወገድ ለአብሮነት መጠናከር እንደሚሰሩም አክለዋል።


መምህር መልካሙ አዲስ በበኩላቸው፤ "ለሀገሬ ምን መስራት አለብኝ? የጠላቶቿ ሴራስ ምንድን ነው? ብሎ የሚመረምር ንቁ ትውልድ የመቅረፅ ሚናችንን ለመወጣት ተግተን እንሰራለን ብለዋል።

በወልዲያ ከተማ አስተዳደር የከንቲባ የህዝብ ግንኙነት አማካሪ አቶ ተስፋዬ ገብሬ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት፤ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ፣ ፍትሃዊና ተዓማኒ ሆኖ እንዲከናወን ተሳታፊዎቹ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡም አሳስበዋል።

በብልፅግና ፓርቲ የምዕራብ ጎንደር ዞን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ እንዳለው ማሩ በበኩላቸው፥ መምህራን በአእምሮና በአካል የዳበረ ትውልድን የመገንባት ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው ብለዋል።

ትውልድን በሳይንስና በቴክኖሎጂ እውቀት በማነጽ ኢትዮጵያ በእድገት ወደ ፊት እንድትጓዝ ለማድረግ መስራት እንዳለባቸውም አመልክተዋል።

መንግስት 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ በሚሰራው ስራ ሁሉ መምህራን ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም