በአዲስ አበባ የወጣቶችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥና ዘላቂነት ያለው የአሰራር ምኅዳር ተፈጥሯል - አቶ ሚሊዮን ማቲዎስ - ኢዜአ አማርኛ
በአዲስ አበባ የወጣቶችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥና ዘላቂነት ያለው የአሰራር ምኅዳር ተፈጥሯል - አቶ ሚሊዮን ማቲዎስ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 2/2018(ኢዜአ)፦በአዲስ አበባ የወጣቶችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥና ዘላቂነት ያለው የአሰራር ምኅዳር መፈጠሩን በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሚሊዮን ማቲዎስ ገለጹ፡፡
ቢሮው "የግል ዘርፍ ተሳትፎ፤ የብቁ ወጣቶች ማንሰራራት ለሀገር ልዕልና" በሚል መሪ ሐሳብ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ለሦስት ተከታታይ ቀናት የሚቆይ ታላቅ የሥራ አውደ ርዕይ ከፍቷል።
በአውደ ርዕዩ ስድስት ሺህ ለሚሆኑ ሥራ ፈላጊዎች የሥራ ዕድል ተጠቃሚነት እንዲሁም ከሁለት መቶ በላይ ቀጣሪ ድርጅቶችም ይሳተፋሉ ተብሏል፡፡
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሚሊዮን ማቲዎስ በመክፈቻው ላይ እንደገለጹት፣ መንግስት ወጣቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪና የገበያውን ፍላጎት ያሟሉ እንዲሆኑ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።
የከተማዋ የ24/7 የሥራ ባህልና ፈጣን ዕድገት ለዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠር ትልቅ መሠረት እየጣለ መሆኑን ጠቅሰው በቴክኖሎጂ የታገዘ የሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓት ተግባራዊ መደረጉንም ጠቁመዋል።
የቢሮው ምክትል ሃላፊ እና የምግብ ዋስትና ዘርፍ ኃላፊ አቶ አስፋው ለገሰ በበኩላቸው ባለፉት ሰባት ወራት በበርካታ ዘርፎች የሥራ ዕድል መፈጠሩን ተናግረዋል፡፡
በዋናነትም የከተማ ግብርና እና ኮንስትራክሽን፣ ኢንዱስትሪና የአገልግሎት ዘርፍ ፣ በቅጥር እና በማኅበር ተደራጅተው የሚሠሩባቸው መስኮች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በዚህም ባለፉት ሰባት ወራት ብቻ ከ287 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን ጠቁመዋል፡፡
በአውደ ርዕዩ ላይ የተገኙት ሥራ ፈላጊዎቹ ሳራ አብደላና ተስፋዬ ደስታው መርሃ ግብሩ ብዙ ቀጣሪዎችን በአንድ ቦታ ለማግኘትና ያለምንም እንግልት ለማመልከት ዕድል እንደፈጠረላቸው ገልጸዋል።
በቀጣሪ ድርጅቶች በኩል የዋርካ ጋርመንት ሥራ አስኪያጅ ትዕግስት ብርሃን እና የኤች ኤንድ ኤ ጋርመንት ተወካይ አቶ ቴዎድሮስ ገብረእግዚአብሔር አውደ ርዕዩ ለድርጅታቸው የሚሆን ብቁ የሰው ኃይል ለማግኘት የሚፈጀውን ጊዜ እንደሚያሳጥርላቸውና ውጤታማነታቸውን እንደሚያሳድግ ገልጸዋል።
ይህ ለሦስት ቀናት የሚቆየው አውደ ርዕይ የከተማዋን የሥራ አጥነት ችግር ለመቅረፍና የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ለማሳደግ እንደ ተጨማሪ አቅም እንደሚሆን ተጠቁሟል፡፡