ቀጥታ፡

ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ለ23 ተጫዋቾች ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 2/2018 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳኅሌ ኢትዮጵያ ከሳኦቶሜ እና ፕሪንሲፔ ጋር ለምታደርገው የ36ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ዝግጅት ለ23 ተጫዋቾች ጥሪ አቀረቡ።

በዚህም መሠረት፤ አቡበከር ኑራ (ከኢትዮጵያ መድን)፣ ፍሬው ጌታሁን (ከድሬዳዋ ከተማ) እና ሰኢድ ሀብታሙ (ከሐዋሳ ከተማ) ጥሪ የተደረገላቸው ግብ ጠባቂዎች ናቸው።

እንዲሁም ዓለምብርሃን ይግዛው (ከመቻል)፣ አሥራት ቱንጆ (ከድሬዳዋ ከተማ)፣ ያሬድ ካሳዬ (ከኢትዮጵያ መድን)፣ አብዱሰላም ዩሱፍ (ከድሬዳዋ ከተማ)፣ ያሬድ ባዬ (ከሲዳማ ቡና)፣ ራምኬል ጀምስ (ከኢትዮጵያ ቡና)፣ ምኞት ደበበ (ከፋሲል ከነማ) እና ግሩም ሀጎስ (ከመቻል) ጥሪ የተደረገላቸው የተከላካይ መስመር ተጫዋቾች ናቸው። 

በአማካይ ክፍል ደግሞ ሀብታሙ ተከስተ (ከፋሲል ከነማ)፣ ጋቶች ፓኖም (ከአል አረቢ ሳዑዲ ዓረቢያ)፣ ብሩክ እንዳለ (ከወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ)፣ ብዙዐየሁ ሰይፉ (ከአዳማ ከተማ)፣ ወገኔ ገዛኸኝ (ከኢትዮጵያ መድን) እና ቢኒያም ዐይተን (ከአዳማ ከተማ) በጥሪው ተካትተዋል።


 

በተጨማሪም በአጥቂ መስመር ቸርነት ጉግሳ (ከመቻል)፣ መስፍን ታፈሰ (ከኢትዮጵያ ቡና)፣ አቡበከር ሳኒ (ከአዳማ ከተማ)፣ ከቤ ብዙነህ (ከነገሌ አርሲ)፣ አቤል ያለው (ከሲዳማ ቡና) እና ከነዓን ማርክነህ (ከአል ሻባብ ኦማን) ጥሪ ቀርቦላቸዋል።

አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳኅሌ ተጫዋቾቹ ከኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 24ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር በኋላ ዝግጅታቸውን እንደሚጀምሩ አስታውቀዋል።

ተጫዋቾቹን ለመመልመል እና ለመምረጥ ጊዜ ተወስዶ መሠራቱንም አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያ የመጀመሪያ ጨዋታዋን ሳኦቶሜ የሜዳ ጨዋታዋን ለማድረግ በመረጠችው ሞሮኮ ኤል አብዲ ስታዲየም መጋቢት 18 ቀን 2018 ዓ.ም ታደርጋለች።

የመልሱ ጨዋታ ደግሞ በድሬዳዋ ስታዲየም መጋቢት 22 ቀን 2018 ዓ.ም እንደሚከናወን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መረጃ አመላክቷል።

36ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በኬንያ፣ ታንዛንያ እና ዑጋንዳ ጣምራ አዘጋጅነት በፈረንጆቹ ሰኔ 2027 ይካሄዳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም