ቀጥታ፡

በሱዳን የቆዩና በተለምዶ አርሚ 70 እየተባሉ የሚጠሩ ከቀድሞ ህወሃት ጎን የነበሩና ትጥቅ የፈቱ አባላት በተሃድሶ ሂደት እያለፉ ነው

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 2/2018(ኢዜአ)፦ በሱዳን የቆዩና በተለምዶ አርሚ 70 እየተባሉ የሚጠሩ ከቀድሞ ህወሃት ጎን የነበሩና ትጥቅ የፈቱ አባላት በተሃድሶ ሂደት እያለፉ እንደሚገኙ የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ገለጸ።

በአዋሽ አርባ ጊዜያዊ የዲሞቢላይዜሽን ማዕከል የተሃድሶ ሥልጠና የተከታተሉ የቀድሞ ታጣቂዎች ሂደቱን አልፈው ወደ ማህበረሰቡ የመቀላቀል መርኃ ግብር እየተካሄደ ነው።


 

የመከላከያ ሠራዊት የሰው ሃብት አመራር ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል አጫሉ ሸለመ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤  የቀድሞ ታጣቂዎች የመረጡት የሰላም መንገድ ለሌሎችም ትምህርት የሚሆን ነው።

መንግስት በቀጣይም በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መሰረት  የሰላም አማራጭን  በመከተል ትጥቅ ፈትተው ለሚመጡ አካላት አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።

የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር ተመስገን ጥላሁን በበኩላቸው፤ የቀድሞ ታጣቂዎችን ወደ ማህበረሰቡ የመመለስ ሥራ ለዘላቂ ሰላም ወሳኝ ነው ብለዋል።

ይህም ሰላምን ለማጽናትና የቀድሞ ታጣቂዎች የልማት ኃይል እንዲሆኑ በማድረግ በኩል ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ ተናግረዋል።


 

ኮሚሽኑ  በትግራይ፣ በአማራ፣ በኦሮሚያ እና በአፋር ክልሎች ከ85 ሺህ በላይ የቀድሞ ታጣቂዎች ትጥቅ በመፍታትና ወደ ማህበረሰቡ በመቀላቀል የሰላምና የልማት ኃይል እንዲሆኑ ማድረጉን አንስተዋል።

የቀድሞ ህወሃትን በመደገፍ የተዋጉና በሱዳን የኢትዮጵያ ድንበር አካባቢ ሲንቀሳቀሱ የቆዩና በተለምዶ አርሚ 70 እየተባለ የሚጠራ ቡድን አባላት ወደ ሀገራቸው ገብተው ለፌዴራል መንግስት በግልጽ ያቀረቡት የዲሞቢላይዜሽን ጥያቄ በመንግስት ተቀባይነት ማግኘቱን አስታውቀዋል።

በዚህም በብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን አማካኝነት በአዋሽ አርባ ጊዜያዊ የዲሞቢላይዜሽን ማዕከል የተሃድሶ ሥልጠና የመስጠትና ሂደቱን አልፈው ወደ ማህበረሰቡ እንዲቀላቀሉ የማድረግ ሥራ መጀመሩን ተናግረዋል። 

በሂደቱም ከ500 በላይ የሚሆኑ ትጥቅ የፈቱ አባላትን በማዕከሉ በመቀበል፣ የስነ ልቦና እና የስነምግባር እንዲሁም የማህበራዊ ጉዳይ ስልጠናዎች እንዲወስዱ መደረጉን ገልጸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም