ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ የገቢና ወጪ የንግድ እንቅስቃሴዎችን በላቀ ብቃት የማሳለጥ ተልዕኮውን አጠናክሮ ቀጥሏል

ድሬዳዋ፤ መጋቢት 2/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ የገቢና ወጪ የንግድ እንቅስቃሴዎችን በላቀ ብቃት የማሳለጥ ተልዕኮውን አጠናክሮ መቀጠሉን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ብሩክ ታዬ (ዶ/ር) ተናገሩ።

የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ 100 ዘመናዊ የከባድ ጭነት ተሽከርካሪዎችን ሥራ አስጀምሯል፡፡

በመንግሥት ከፍተኛ ድጎማ የሚቀርበውን ነዳጅ ከተተመነለት የዋጋ መጠንና የግብይት ሰንሰለት ውጪ በሚሸጡ ሕገወጦች ላይ የተጠናከረ እርምጃ መውስድ ተጀምሯል


 

የከባድ መኪናዎችን ቁልፍ ከሲኖ ትራክ ኩባንያ የኢትዮጵያ ተወካይ ተረክበው ስራ ያስጀመሩት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ብሩክ ታዬ (ዶ/ር) እና የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አብዱልበር ሸምሱ ናቸው።

ብሩክ ታዬ (ዶ/ር) በወቅቱ እንዳሉት፤ በሆልዲንጉ ስር ከሚገኙ ተቋማት አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ የባህርና ትራንስፖርት ሎጂስቲክስ የኢትዮጵያን ብልፅግናና ዕድገት በሚመጥን ከፍታ ኃላፊነቱን እንዲወጣ በቅንጅት እየተሰራ ነው።


 

የኢትዮጵያን የወጪና ገቢ እንቅስቃሴዎች ለማሳለጥ ወሳኝ አበርክቶ ያለውን ድርጅት በዘመናዊ አደረጃጀትና አሰራር በማገዝ የላቀ እና የተሳለጠ አገልግሎት እንዲሰጥ እየተሰሩ የሚገኙ ተግባራት ውጤታማ መሆናቸውን ገልፀዋል።

በዛሬው ዕለት ወደ ስራ የገቡት 100 ዘመናዊ ከባድ መኪኖች የዚሁ ማሳያ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ በቀጣይም ኢትዮጵያ ያላትን የተፈጥሮ ጋዝ የሚጠቀሙ 100 ዘመናዊ ከባድ ተሸከርካሪዎች ወደ ስራ ለማስገባት ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።

እየተሰሩ ያሉ ተግባራት የጭነት ተሽከርካሪ ዕጥረትን በመፍታት በዘርፉ ተመራጭ የአፍሪካ ድርጅት የመሆንን ጉዞ የሚያሳኩ መሆኑን በመግለፅ።

ለድርጅቱ  የሚደረገው ድጋፍና ትኩረት እንደሚጠናከር ጠቅሰው ወደ ስራ የገቡት የከባድ ጭነቶቹ አሽከርካሪዎች የኢትዮጵያን አምባሳደርነት ተልዕኳቸውን በታላቅ ብቃትና ሙያዊ ስነምግባር እንዲወጡ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዋና ስራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አብዱልበር ሸምሱ በበኩላቸው፤ ለድርጅቱ የተሰጠው ትኩረትና ድጋፍ የወጪና የገቢ እንቅስቃሴዎችን በላቀ ብቃትና ቁርጠኝነት ከዳር ለማድረስ እያስቻለ  መሆኑን ተናግረዋል።


 

ዛሬ ወደ ስራ የገቡት ዘመናዊ የጭነት ተሸከርካሪዎች የድርጅቱን አቅም በከፍታ በማሳደግ ወሳኝ አበርክቶ እንደሚኖራቸው ጠቅሰዋል።

ዘመናዊ ዲጂታል አሰራርን በመዘርጋት ሂደት የሚያጋጥሙ እንግልቶችን ለማስቀረት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልፀው በቀጣይ የድርጅቱን አገልግሎቶች በደረቅ ወደብ ብቻ ሳይሆን ቤት ለቤት ተደራሽ በማድረግ የደንበኞቹን እርካታ ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በስነስርዓቱ ላይ የተገኙት የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ቡህ፤ ድርጅቱ በድሬዳዋ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቱ በሚገኘው የወደብና ተርሚናል አገልግሎት እያከናወናቸው ያሉ ስራዎች ድሬዳዋን የንግድ፣ የኢንዱስትሪ እና የሎጂስቲክስ 'ሃብ' የማድረግ ሂደትን በማሳካት ወሳኝ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ገልጸዋል።


 

ከኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ጋር የተነበበ እና የተቀናጀ ስራ በመስራት የኢትዮጵያን የብልጽግና ጉዞ ለማሳካት በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል ።

ዛሬ በተካሄደው የከባድ ጭነት ተሽከርካሪዎች ስራ ማስጀመሪያ መርሃግብር ላይ የተገኙት የከባድ ጭነት አሽከርካሪዎች በበኩላቸው ፤ኢትዮጵያን የሚመጥን ከባድ አገራዊ ኃላፊነትን ለመወጣት በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም