ቀጥታ፡

የሲዳማ ዘመን መለወጫ "ፊቼ ጫምባላላ" በመጪው ቅዳሜና እሁድ በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራል

ሃዋሳ ፤ መጋቢት 2/2018 (ኢዜአ)፦የሲዳማ ዘመን መለወጫ "ፊቼ ጫምባላላ" በዓል በመጪው ቅዳሜና እሁድ በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚከበር የሲዳማ ክልል ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ አስታወቀ፡፡

ቢሮው የበዓሉን አከባበር በማስመልከት ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥቷል፡፡

የቢሮ ሃላፊው አቶ ጃጎ አገኘሁ እንደተናገሩት፤ የሰላምና የመቻቻል እሴትን በውስጡ የያዘው "ፊቼ ጫምባላላ" የሲዳማ አባቶች በሀገር በቀል እውቀት ዘመንን መቁጠር የሚቻልበትን ጥበብ ለትውልድ ያቆዩት ነው።

በዓሉ በዓለም የማይዳሰስ ቅርስነት መመዝገቡን አስታውሰው፣ ዘንድሮም ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ በመጪው ቅዳሜና እሁድ እንደሚከበርና ለዚህም ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።

በዓሉ የተጣሉ እንዲታረቁ በማድረግ የሰላም፣ የአብሮነትና የመከባበር እሴት የሚጎለብትበት መሆኑንም ነው የጠቆሙት።

የፊቼ ጫምባላላ በዓል በአዲስ መንፈስ፣ በአዲስ እሳቤና በአዲስ ተስፋ በውስጡ የያዛቸውን እሴቶች በሚያጠናክር መልኩ እንደሚከበርም ተናግረዋል።

ለበዓሉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መጠናቀቃቸውን የገለጹት አቶ ጃጎ፣ ባህላዊ እሴቱን የሚያጎለብቱ ካርኒቫሎችም በቀጣይ ቀናት እንደሚካሄዱ አመልክተዋል።

የቱሪዝምና የአገልግሎት ማዕከል የሆነቸው ሃዋሳ ከተማ ከመቼውም ጊዜ በላይ በኮሪደር ልማት መድመቋ በዓሉን የተለየ እንደሚያደርገው ጠቁመው፣ በዓሉ ክልሉንና ከተማዋን ለማስተዋወቅ ትልቅ ዕድል ነው ብለዋል።

''ኑ ወደ ሲዳማ እንሂድ'' በሚል መሪ ሃሳብ ታዋቂ የኪነ ጥበብ ሰዎችና አርቲስቶች የተሳተፉበት የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎችንና መልካም እሴቶችን የማስተዋወቅ ሥራ እንደሚሰራም አመልክተዋል።

በዓሉ የሲዳማ ብቻ ሳይሆን የመላው ዓለም ቅርስ መሆኑን በመግለጽ በዓሉን ለማክበር ወደ ከተማው የሚገቡ እንግዶችን የከተማዋ ነዋሪዎች በኢትዮጵያዊ ጨዋነት ተቀብለው እንዲያስተናግዱ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም