የቡና ምርት ዋጋ ይጨምራል በሚል ኢ-ሳይንሳዊ የገበያ ትንበያ ምርት ያከማቹ አካላት ምርታቸውን ለማዕከላዊ ገበያ ማቅረብ አለባቸው - ግብርና ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የቡና ምርት ዋጋ ይጨምራል በሚል ኢ-ሳይንሳዊ የገበያ ትንበያ ምርት ያከማቹ አካላት ምርታቸውን ለማዕከላዊ ገበያ ማቅረብ አለባቸው - ግብርና ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 2/2018(ኢዜአ)፦ የቡና ምርት ዋጋ ይጨምራል በሚል ኢ-ሳይንሳዊ የገበያ ትንበያ ምርት ያከማቹ አካላት ምርታቸውን ለማዕከላዊ ገበያ ማቅረብ እንዳለባቸው የግብርና ሚኒስቴር አሳሰበ።
የግብርና ሚኒስቴር የበጀት ዓመቱ የስድስት ወራት የቡና ዘርፍ ስኬቶች፣ በዓለም አቀፍ የግብይት አዝማሚያዎችና መወሰድ ስላለባቸው ጥንቃቄዎች ዙሪያ መግለጫ ሰጥቷል።
መግለጫውን የሰጡት የግብርና ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈፃሚ ይመር ዳውድ፤ ኢትዮጵያ ቡናን በጥራትና በመጠን በማምረትና ለዓለም ገበያ በማቅረብ የተሻለ ገቢ ማግኘቷን አስታውሰዋል።
የቡናን ዕሴት ሰንሰለት በማሳለጥና ምርታማነትን በማሳደግ የተመዘገቡ ስኬቶች ለዘርፉ እመርታዊ ገቢ ከፍተኛውን ድርሻ መውሰድ እንዳስቻለ አስረድተዋል።
በዚህም ባለፉት ዓመታት የቡና ምርት ለኢትዮጵያ የገቢ ዕድገት ያለውን ጠንካራ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ በተግባር ማሳየት እንደቻለ አንስተዋል።
የዓለም የቡና ገበያ በከፍተኛ ሁኔታ ዝቅ ብሏል ያሉት ሥራ አስፈፃሚው፤ በዚህም አምራቾች ሊደርስ የሚችልን ኪሳራ ታሳቢ በማድረግ ምርታቸውን ለማዕከላዊ ገበያ እንዲያቀርቡ አሳስበዋል።
ቡና አምራቾችና ላኪዎችም በተሳሳተ ስሌት ምርትን ከማከማቸት ይልቅ ወቅታዊ የገበያ ሁኔታን ታሳቢ በማድረግ የእራሳቸውንና የሀገርን ገቢ ከሚጎዳ ተግባር መቆጠብ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
ይህንን ለመከላከል የተቋቋመው ግብረ ኃይል ከክልል ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ዋጋ ይጨምራል በሚል የቡና ምርት ይዘው ባከማቹ አካላት ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ አስታውቀዋል።
ኢ-ሳይንሳዊ በሆነ የገበያ ትንበያ ላይ ተመስርተው ከዘርፉ ገቢ እንዳይገኝ የሚያደርጉ አካላትም በሕግ ተጠያቂ እንደሚሆኑ ተናግረዋል።