ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ የ18ኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን ውሎ 

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 2/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ 18ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ውሎ ሁለት ጨዋታዎች ይካሄዳሉ።

ከረፋዱ 4 ሰዓት ላይ ሸገር ከተማ ከአዲስ አበባ ከተማ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ይጫወታሉ። 

ሸገር ከተማ በሊጉ ባደረጋቸው 17 ጨዋታዎች በ11ዱ አሸንፎ በአምስቱ ተሸንፎ አንድ ጊዜ አቻ ወጥቷል። በ17ቱ ጨዋታዎች 27 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 18 ጎሎች ተቆጥረውበታል።  ቡድኑ በ34 ነጥብ አምስተኛ ደረጃን ይዟል። 

ተጋጣሚው አዲስ አበባ ከተማ በሊጉ 17 ጨዋታዎች አከናውኖ ሁለት ጊዜ ድል ሲቀናው 13 ጊዜ ተሸንፏል። በቀሪ ሁለት ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቷል። ዘጠኝ ግቦችን ሲያስቆጥር 35 ጎሎችን አስተናግዷል።

አዲስ አበባ ከተማ በስምንት ነጥብ የመጨረሻውን 14ኛ ደረጃ ይዟል። 

መርሐ-ግብሩ ሸገር ከተማ ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ፣  አዲስ አባ ከተማ በሊጉ ሶስተኛ ድሉን ለማስመዝገብ የሚያደርጉት ነው። 


 

በሌላኛው መርሐ-ግብር አዳማ ከተማ ከይርጋጨፌ ቡና ከቀኑ 7 ሰዓት ላይ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። 

አዳማ ከተማ እስከአሁን በሊጉ ያሸነፋቸው ጨዋታዎች አራት ናቸው። ስምንት ጊዜ ሲሸነፍ አምስት ጊዜ አቻ ወጥቷል። 12 ግቦችን ሲያስቆጥር 27 ጎሎችን አስተናግዷል። ቡድኑ በ17 ነጥብ ዘጠነኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። 

ተጋጣሚው ይርጋጨፌ ቡና በበኩሉ 17 ጨዋታዎችን አድርጎ ሁለት ጊዜ ሲያሸንፍ በ10ሩ ተሸንፏል። በአምስት ጨዋታዎች ነጥብ ጥሏል። በጨዋታዎቹ ላይ ስምንት ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 25 ጎሎች ተቆጥረውበታል። 

አዲስ አዳጊው ይርጋጨፌ ቡና በ11 ነጥብ 11ኛ ደረጃን ይዟል። 

በ17ኛ ሳምንት አዳማ ከተማ ከአርባምንጭ ከተማ ጋር ያለ ግብ አቻ ተለያይቷል። ይርጋጨፌ ቡና በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የ3 ለ 1 ሽንፈት አስተናግዷል።

ሁለቱም ቡድኖች ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም