ዓለም በጉጉት የሚጠብቀው የሪያል ማድሪድ እና ማንችስተር ሲቲ ተጠባቂ ጨዋታ - ኢዜአ አማርኛ
ዓለም በጉጉት የሚጠብቀው የሪያል ማድሪድ እና ማንችስተር ሲቲ ተጠባቂ ጨዋታ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 2/2018 (ኢዜአ)፦ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ጥሎ ማለፍ ዛሬ አራት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።
ምሽት 5 ሰዓት ላይ ሪያል ማድሪድ ከማንችስተር ሲቲ በበርናባው ስታዲየም የሚያደርጉት ጨዋታ የዓለም እግር ኳስ አፍቃሪያንን ቀልብ ስቧል።
ሪያል ማድሪድ በጥሎ ማለፍ ማጣሪያው ቤኔፊካን በድምር ውጤት 3 ለ 1 በማሸነፍ 16 ውስጥ ገብቷል።
ማንችስተር ሲቲ በ16 ነጥብ ስምንተኛ ደረጃን ይዞ ጥሎ ማለፉን ተቀላቅሏል።
ሁለቱ ቡድኖች በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ሲገናኙ የአሁኑ ለ16ኛ ጊዜ ነው።
ከዚህ ቀደም በነበራቸው የ15 ጊዜ ግንኙነት ቡድኖች በተመሳሳይ አምስት ጊዜ አሸንፈዋል። በቀሪ አምስት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል።
ሪያል ማድሪድ በ15ቱ ጨዋታዎች ላይ 26 ግቦችን ሲያስቆጥር ማንችስተር ሲቲ 25 ጎሎችን ከመረብ ላይ አሳርፏል።
ቡድኖቹ ለመጨረሻ ጊዜ የተገናኙት እ.አ.አ በ2024/25 የውድድር ዓመት በተመሳሳይ በጥሎ ማለፍ ዙር ላይ ነበር።
በወቅቱ ሪያል ማድሪድ በደርሶ መልስ ውጤት 6 ለ 3 በማሸነፍ ሩብ ፍጻሜውን ተቀላቅሏል።
በአውሮፓ መድረክ ላለፉት ተከታታይ ዓመታት እየተፎካከሩ የሚገኙት ሁለቱ ክለቦች ዛሬ የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል።
ሪያል ማድሪድ 15 ጊዜ ዋንጫውን በማንሳት የውድድሩ ስኬታማ ክለብ ነው። ማንችስተር ሲቲ አንድ ጊዜ የዋንጫው ባለቤት ሆኗል።
የ44 ዓመቱ ጣልያናዊ ማውሪዚዮ ማሪያኒ ተጠባቂውን ጨዋታ በዋና ዳኝነት ይመሩታል።
በሌላኛው መርሐ-ግብር ፒኤስጂ ከቼልሲ ምሽት 5 ሰዓት ላይ በፓርክ ደ ፕሪንስ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው።
ፒኤስጂ የወቅቱ የውድድሩ አሸናፊ ነው። ቼልሲ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን አንድ ጊዜ አንስቷል።
ሁለቱ ክለቦች ጠንካራ ፍልሚያ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ምሽት 2 ሰዓት ከ45 ላይ ባየር ሌቨርኩሰን ከአርሰናል በቤይ አሬና ስታዲየም ይጫወታሉ።
የጀርመኑ ባየር ሌቨርኩሰን በጥሎ ማለፍ ማጣሪያው የግሪኩን ኦሎምፒያኮስን በደርሶ መልስ 2 ለ 0 በማሸነፍ ጥሎ ማለፍ ገብቷል።
አርሰናል በውድድሩ የሊግ ምዕራፍ ያደረጋቸውን ስምንት ጨዋታዎች በማሸነፍ በ24 ነጥብ አንደኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁ የሚታወስ ነው።
ቦዶ ግሊምት ከስፖርቲንግ ሊዝበን ምሽት 5 ሰዓት ላይ በአስፕማይራ ስታዲየም ይጫወታሉ።
የኖርዌው ቦዶ ግሊምት በጥሎ ማለፍ ማጣሪያው ኢንተር ሚላንን በድምር ውጤት 5 ለ 2 አሸንፏል።
የፖርቹጋሉ ስፖርቲንግ ሊዝበን በ16 ነጥብ ሰባተኛ ደረጃን ይዞ በቀጥታ ጥሎ ማለፉን መቀላቀሉ ይታወቃል።