ቀጥታ፡

ኢትዮ ኤሌክትሪክ መሪነቱን ያጠናከረበት ወሳኝ ድል አስመዘገበ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 1 /2018 (ኢዜአ)፦‎ በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ 18ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ኢትዮ ኤሌክትሪክ ልደታ ክፍለ ከተማን 4 ለ 2 አሸንፏል።

በአበበ ቢቂላ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ዳግማዊት ሰለሞን ሶስት ግቦችን በማስቆጠር ሀትሪክ ሰርታለች።

ማህሌት ምትኩ ቀሪዋን ጎል ለኢትዮ ኤሌክትሪክ ከመረብ ላይ አሳርፋለች።

ሄለን ጌታቸው እና ይታገሱ ተገኘወርቅ  ለልደታ ክፍለ ከተማ ግቦቹን አስቆጥረዋል።

ሀትሪክ የሰራችው ዳግማዊት ሰለሞን የጨዋታው ኮከብ ሆና ተመርጣለች።



በሊጉ 16ኛ ድሉን ያስመዘገበው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ49 ነጥብ የሊጉን መሪነት አጠናክሯል።

ከተከታዩ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ያለው ልዩነት በሁለት ነጥብ ቀጥሏል።

በአንጻሩ በውድድር ዓመቱ 11ኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው ልደታ ክፍለ ከተማ በ15 ነጥብ 10ኛ ደረጃን ይዟል።

የኢትዮ ኤሌክትሪኳ አጥቂ ዳግማዊት ሰለሞን በሊጉ ያስቆጠረቻቸውን ግቦች ወደ 22 ከፍ በማድረግ የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቷን አጠናክራለች።

ዛሬ በተደረገ የ18ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ጨዋታ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቦሌ ክፍለ ከተማን 2 ለ 1 አሸንፏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም