ቀጥታ፡

በጾም ወቅት የተቸገሩትን በመርዳትና በጎ ሥራን በማከናወን የሚታየው መደጋገፍ ሊጠናከር ይገባል-የሃይማኖት አባቶች

ቦንጋ ፤የመጋቢት 1/2018 (ኢዜአ) ፦በአቢይና በታላቁ ረመዳን የጾም ወቅት የተቸገሩትን በመርዳት፣ ያለን በማካፈልና በጎ ሥራዎችን በማከናወን የምናሳየውን መደጋገፍ የሁሌም ተግባር ልናደርገው ይገባል ሲሉ የሃይማኖት አባቶች ገለጹ።

በሃይማኖት ብዝሀነት የምትታወቅ ኢትዮጵያ የተለያዩ ሃይማኖቶች ለዘመናት አብረው ተቻችለውና ተከባበርው የኖሩባት ሀገር ናት።

ሀገራዊ አንድነት እና ማህበራዊ ትስስርን ማጠናከር የሀይማኖቶች አብሮ የመኖር ውጤት ነው። 

የአቢይ ጸም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት፤ ታላቁ የረመዳን ጾም ደግሞ በእስልምና እምነትና ተከታዮቻቸው ዘንድ ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው ናቸው።

እንደአሁኑ ክርስቲያኑም ሆነ ሙስሊሙ በአንድ ጊዜ ሲጾሙ ደግሞ በሃይማኖቶቹ መካከል ያለው የአንድነትና የመከባበር መንፈስ ይበልጥ ይጠናክራል። 

አጻሟቱ ካላቸው ሃይማኖታዊ ፋይዳ በሻገር ለሀገርና ለህዝቦች አንድነት፣ ለማህበራዊ ትስስር እና እርስ በርስ መደጋገፍ ጠቀሜታቸው የጎላ መሆኑን የየእምነቶቹ አባቶች ይገልጻሉ። 

በቦንጋ ከተማ ኢዜአ ያነጋገራቸው የኦርቶዶክስና የእስልምና እምነት አባቶች እንደገለፁት የአቢይና የረመዳን ፆም ወቅት መረዳዳትና መተሳሰብ የሚጎላበት ነው።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የሀይማኖት አባት መጋቤ ሀይማኖት እሸቱ በላይ እንዳሉት፣ አቢይ ፆም በእምነቱ ተከታዮችና በቤተከርስቲያኒቷ ዘንድ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነው።

ፆም ከምግብና መጠጥ ብቻ መከልከል ሳይሆን ከክፉ ሀሳብና ተግባር መራቅ ጭምር መሆኑን አንስተው የጾም ወቅትን ለሀገርና ለህዝብ ሰላም አበክሮ ከመጸለይ ባለፈ በመተሳሳብ፣ በመደጋገፍና በፍቅር ማሳለፍ እንደሚገባ ገልፀዋል።

በመሆኑም የእምነቱ ተከታዮች የተቸገሩትን በመርዳት፣ ካለ ላይ በማካፈልና በጎ ተግባራትን በማጠናከር ማሳለፍ እንዳለባቸው ጠቅሰው፣ እነዚህን መልካም ተግባራት በፆም ወቅት ብቻ ሳይሆን የሁሌም ባህል ልናደርጋቸው ይገባል ብለዋል።

ያለምንም ልዩነት ከሁሉም ጋር በፍቅርና በአንድነት መኖር እንደሚገባ ጠቁመው፣ ከመለያየትና ከክፉ ነገር በመራቅ ለሀገር ሰላምና ልማት ተግቶ መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል።

የቦንጋ አንሷር መስጂድ ኢማም ሼህ ኢብራሒም አባጀበል በበኩላቸው፣ ታላቁ የረመዳን ወር በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ በጉጉት የሚጠበቅ፤ ከጾምና ጸሎት ባለፈ አንድነትና ፍቅርየሚጎላበት ነው ብለዋል።

በእስልምና እምነት አብሮነት፣ መረዳዳትና መቀራራብን ማጠናከር ትልቅ ቦታ እንዳለው ገልጸው፣ ህዝበ ሙስሊሙ እነዚህን መልካም ተግባራት ከረመዳን ወር በኋላም ይበልጥ ማጠናከር አለበት ብለዋል።  

ረመዳን የሰላም ወር በመሆኑ ህዝበ ሙስሊሙ ለሀገር ሰላም አብዝቶ ከመጸለይ ባለፈ፣ እርስ በርስ መደጋገፍን በማሳደግ አብሮነቱን ማጠናከር እንዳለበት አስገንዝበዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም