ቀጥታ፡

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከግሉ ኢንቨስትመንት ዘርፍ ጋር የተጀመረው ቅንጅታዊ ስራ ይጠናከራል - ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ

ወላይታ ሶዶ፤ መጋቢት 1/2018(ኢዜአ)፦ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ባለፉት ዓመታት የተመዘገበውን ለውጥ ለማስቀጠል ከግሉ ኢንቨስትመንት ዘርፍ ጋር የተጀመረው ቅንጅታዊ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ተናገሩ።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኢንቨስትመንት ኮሚሽን "በተቀናጀና ቀጣይነት ባለው የድጋፍ ማዕቀፍ አምራቿንና ምርታማዋን ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እንፈጥራለን" በሚል መሪ ሃሳብ ክልል አቀፍ የኢንቨስትመንት ፎረም በወላይታ ሶዶ ከተማ እያካሄደ ይገኛል።


 

በፎረሙ የተገኙት ርዕሰ መስተዳድሩ በኢንቨስትመንት ዘርፉ የሚስተዋሉ ማነቆዎችን በመቅረፍ አልሚ ባለሃብቶችን ማበረታታትና መደገፍ እንደሚገባ ገልጸዋል።

በክልሉ ባለፉት ዓመታት የተመዘገበውን ለውጥ ለማስቀጠል ከግሉ ኢንቨስትመንት ዘርፍ ጋር በቅንጅት የተጀመረው ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

ክልሉ ያለውን ዕምቅ የኢንቨስትመንት አቅም በመጠቀም የሰላም፣ የመቻቻልና የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ በተጀመረው ጥረት የግሉ ባለሀብት ሚና ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም ባሉን አቅሞችና ዕድሎች ዙሪያ በመወያየት ክልሉ ከዘርፉ ተገቢውን ጥቅም ማግኘት እንዲችል የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኙም ገልጸዋል።


 

የክልሉ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር አፀደ አይዛ በበኩላቸው በክልሉ 82 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ 1ሺህ 826 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ወደ ስራ ገብተው በርካቶችን ተጠቃሚ እያደረጉ መሆናቸውን አንስተዋል።

ክልሉ ከተመሰረተ በኃላ ከ49 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ 536 የኢቨስትመንት ፕሮጀክቶች በኢንቨስትመንት ቦርድ ፈቃድ ተሰጥቷቸው ወደ ስራ መግባታቸውን ገልጸዋል፡፡

ፕሮጀክቶቹ ለስራ እድል ፈጠራ፣ ለኢኮኖሚ እድገትና ለማህበራዊ አገልግሎት መስፋፋት ጉልህ ሚና እያበረከቱ መሆኑን ገልጸው በክልሉ ያለውን ምቹ ሁኔታ ተጠቅመው ማልማት ለሚፈልጉ ባለሃብቶች ተገቢው ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም