በድሬዳዋና አካባቢው እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎች የመንግስትን የልማት ቁርጠኝነት በተግባር ያሳዩ ናቸው- ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
በድሬዳዋና አካባቢው እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎች የመንግስትን የልማት ቁርጠኝነት በተግባር ያሳዩ ናቸው- ነዋሪዎች
ድሬዳዋ ፣ መጋቢት 1/2018(ኢዜአ)፡- በድሬዳዋና አካባቢው እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎች የመንግስትን የልማት ቁርጠኝነት በተግባር ያሳዩ መሆናቸውን ነዋሪዎች ተናገሩ።
በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው እና ሌሎች የመንግስት ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች በድሬዳዋ እና አካባቢዋ የተለያዩ የልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል።
በድሬዳዋ አስተዳደር ከተመለከቷቸው የልማት ስራዎች መካከል በገበታ ለትውልድ መጽሐፍ ሽያጭ የተገነባው እመርታ ዘመናዊ ቤተ መጻህፍት፣ ድሬዳዋ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት፣ የኮሪደር ልማት፣ የከተማ መልሶ ግንባታና በገንደ ሪጌ የገጠር መንደር የፍራፍሬ ልማት ይገኙበታል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከጉብኝቱ በኋላ ባስተላለፉት መልእክት፤ የበለፀገች ሀገር ለትውልድ ለማስተላለፍ ዛሬ የተሰነቀውን ርዕይ ወደ መሬት በማውረድ መስራት እንደሚገባ አንስተዋል።
በዚህም መሰረት በድሬዳዋ እና አካባቢው እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎች ተስፋ ሰጪ ጅምሮች መሆናቸውን ጠቅሰው ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት መሆኑን አጽኖት ሰጥተዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጉብኝት በተመለከተ ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የድሬዳዋ ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች በመንግስት ብርቱ ጥረት በሁሉም ረገድ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎች ትልቅ ተስፋ የሰነቅንባቸው ናቸው ብለዋል።
ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል ወይዘሮ አረክሰን መሐመድ፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት በአካባቢው የተከናወኑ ስራዎችን በቀጥታ መገምገም ያስቻለ በመሆኑ ለአመራሩም ይሁን ለህዝቡ ለቀጣይ ብርታት የሚሰጥ ነው ብለዋል።
በድሬዳዋ እና አካባቢው እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎች የመንግስትን የልማት ቁርጠኝነት በተግባር ያሳዩ መሆናቸውን ያነሱት ነዋሪዋ ለዘላቂ ስኬታማነታቸው የበኩላችንን እንወጣለን ሲሉ ተናግረዋል።
ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ አብዱረህማን አህመድ፤ በለውጡ ዓመታት በድሬዳዋና አካባቢው ሁላችንንም ተጠቃሚ ያደረጉን የተለያዩ የልማት ስራዎች ተከናውነዋል ብለዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝትም ለእነዚህ የልማት ስራዎች እውቅና የሚሰጥ ነው ያሉት አቶ አብዱረህማን፤ ቀጣይነት እንዲኖራቸው በትብብር እንሰራለን ሲሉ ተናግረዋል።
የድሬዳዋ ከተማ ነዋሪ አቶ መሐመድ አሊ፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝትና ከማህበረሰቡ ጋር ያደረጉት ቆይታ በነዋሪው ዘንድ ትልቅ ደስታና ፍቅር የፈጠረ መሆኑን በመግለጽ አስተዳደሩና ነዋሪው ተቀናጅተው በኮሪደርና በሌሎች ልማቶች ያሳኩትን ውጤት ይበልጥ ለማስቀጠል ሞራል የሚፈጥር ነው ብለዋል።
በገንደ ሪጌ የገጠር ቀበሌ የሚኖሩት ወይዘሮ አርዶ መሐመድ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቀበሌው ተገኝተው የብርቱካን ልማት መመልከታቸው አርሶ አደሩን የበለጠ ተግቶ ለመስራት ያነሳሳና ደስታ የፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።
ሌላኛው የአካባቢው ነዋሪ አቶ ኢሊያስ ደለለኝ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የድሬዳዋን ለውጥ መጎብኘታቸው በቀጣይ ለድሬዳዋ ልማትና እድገት ይበልጥ በትጋት እንድንሰራ የሚያደርግ ነው ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከድሬዳዋ በተጨማሪ በሀረር ከተማና አካባቢው የተለያዩ የልማት ስራዎችን ተዘዋውረው መጎብኘታቸው ይታወቃል።