ምርጫ ህዝብ የስልጣን ባለቤት መሆኑ በተግባር የሚረጋገጥበት ነው - ኢዜአ አማርኛ
ምርጫ ህዝብ የስልጣን ባለቤት መሆኑ በተግባር የሚረጋገጥበት ነው
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 1/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርጫ የመንግሥት የስልጣን ምንጭ ህዝብ መሆኑን በተግባር የሚረጋገጥበት መሆኑን ምሁራን ገለጹ።
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ግንቦት 24/2018 ዓ.ም ድምፅ በሚሰጥበት የዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ ከየካቲት 28/2018 ዓ.ም ጀምሮ በመከናወን ላይ ነው።
መራጮችም በዲጂታል "ምርጫዬ" መተግበሪያና በየምርጫ ጣቢያዎች በአካል በመገኘት ድምፅ መስጠት የሚያስቻለቸውን የምርጫ ካርድ በመውሰድ ላይ ይገኛሉ።
በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ 47 ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች 10ሺህ 934 ዕጩዎችን በማስመዝገብ በመገናኛ ብዙኅን አማካኝነት የምርጫ ምልክትና የርዕዮተ ዓለማቸውን በማስተዋወቅ ላይ ናቸው።
የሕግና የምጣኔ ሃብት ምሁራን ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ምርጫ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታን በማጠናከር ዜጎች ሕገ-መንግስታዊ መብታቸውን የሚጠቀሙበት መድረክ ነው።
የሕግ መምህርና ተመራማሪ ማናየ ዘገየ(ዶ/ር)፤ ምርጫ የመንግሥት የስልጣን ምንጭ ህዝብ መሆኑን በተግባር የሚያረጋግጥ የጋራ መድረክ ነው ብለዋል።
ከዚህ ቀደም በተካሄዱ ምርጫዎች ላይ ውስንነቶች ቢስተዋልባቸውም መራጩ ዜጋ የሚሰጠው ድምፅ የመንግሥት ስልጣን ህዝብ መሆኑን በተግባር ሲታይ መቆየቱን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያውያንም ዘንድሮ በሚከናወነው ጠቅላላ ምርጫ ይበጀኛል ለሚሉት ፓርቲ ድምፅ በመስጠት ለስኬታማ የስልጣን ሽግግር ውጤታማነት ሕገ-መንግስታዊ መብታቸውን ሊጠቀሙበት እንደሚገባ ገልጸዋል።
በምርጫ ሂደቱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችና መራጩ ህዝብ ለምርጫው ነፃ፣ ሰላማዊና ፍትሕዊነት ገንቢ አስተዋጽኦ ማበርከት እንደሚኖርባቸውም አስገንዝበዋል።
ሌላኛው የምጣኔ ሀብት መምህርና ተመራማሪ ገመቺስ መርሻ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ሀገራዊ ምርጫ የምቹ ፖለቲካ ምኅዳርን በማስፋት ለዴሞክራሲ ዕድገት ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው ብለዋል።
የፖለቲካ ምኅዳርን በማስፋት ዜጎች በምርጫ ሂደት ሕገ-መንግስታዊ የመምረጥና መመረጥ መብታቸውን የሚያንጸባርቁበትን ሁኔታ ለመፍጠርም የምርጫ ተዋናዮች ትብብር ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርጫ የህዝብን አንድነትና የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም በማስቀደም የጋራ ተጠቃሚነትን ለማስጠበቅ በኃላፊነት መንፈስ መስራት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።
ምርጫ የዴሞክራሲ ባህል መገንቢያ ቁልፍ መሳሪያ ነው ያሉት ምሁራኑ፤ ነፃ፣ ገለልተኛና ፍትሕዊ ምርጫን ማስፈጸም ሲቻል የህዝብና መንግሥትን ጤናማ መስተጋብር ለመፍጠር መሠረት መሆኑን አስገንዝበዋል።