የሰብዓዊ ድጋፍ ስራን በሉዓላዊነት ማዕቀፍ ውስጥ በመምራት በኩል ተጨባጭ ውጤቶች እየተመዘገቡ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሰብዓዊ ድጋፍ ስራን በሉዓላዊነት ማዕቀፍ ውስጥ በመምራት በኩል ተጨባጭ ውጤቶች እየተመዘገቡ ነው
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 1/2018(ኢዜአ)፦ የሰብዓዊ ድጋፍ ስራን በሉዓላዊነት ማዕቀፍ ውስጥ በመምራት በኩል ተጨባጭ ውጤቶች እየተመዘገቡ መሆኑን የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም(ዶ/ር) ገለጹ።
አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም(ዶ/ር) ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ከአደጋ በፊት የመዘጋጀትና የችግር ቀንን በራስ አቅም የመወጣት አዲስ ስርዓት ዘርግታ ወደ ስራ ገብታለች።
ስራው ሀገራዊ የፈንድ ስርዓት መዘርጋት ሲሆን ይህም መላው ማህበረሰብ የሚሳተፍበት ከችግር በፊት ተዘጋጅቶ መጠበቅ የሚያስችል ነው ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ምላሽ ፈንድ ተደራጅቶ ሀብት የማሰባሰብ ስራ በስፋት እየተከናወነ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።
ሌላኛው የመጠባበቂያ ክምችት ስርዓት መዘርጋት መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም ከቤተሰብ ጀምሮ እስከ ማህበረሰብ ደረጃ ለክፉ ቀን በበጎ ቀን መዘጋጀት በሚለው መርህ እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ለዚህም ይረዳ ዘንድ የመጋዘን አደረጃጀቶችን በሳይንሳዊ ስሌት በፌዴራል እና በክልሎች የመገንባት ስራ እየተከናወነ እንዳለም ነው የተናገሩት።
ባለፉት ሁለት ዓመታት አስር ክልሎች ከፌዴራል መንግሥት ምንም አይነት ሰብዓዊ ድጋፍ ሳይጠብቁ በራሳቸው አቅም እንዲሸፍኑ መደረጉን ጠቅሰዋል።
ቀደም ሲል ለምግብ እርዳታ እህል ከውጭ ለማስገባት ይወጣ የነበረውን እስከ ሁለት ቢሊየን ዶላር የሚደርስ ወጪ በሀገር ውስጥ ምርት መተካት መቻሉን አስረድተዋል።
በተለያዩ አካባቢዎች የሚስተዋሉ የመረዳዳት እሴቶች ወደ ተቋማዊ አሰራር በማደግ ላይ መሆናቸውንም ነው ኮሚሽነሩ የተናገሩት።
ይህ የለውጥ ስራ የቤተሰብ ኃላፊነትንና የማህበረሰብ አጋርነትን በማጠናከር የሀገርን አይበገሬነት የመገንባት ትልቅ መሰረት መሆኑን አረጋግጠዋል።