ሐዋሳ ከተማ ከመቀሌ 70 እንደርታ ጋር ይጫወታል - ኢዜአ አማርኛ
ሐዋሳ ከተማ ከመቀሌ 70 እንደርታ ጋር ይጫወታል
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 1 /2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 23ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ዛሬ በሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ይጠናቀቃል።
ከቀኑ 9 ሠዓት ላይ ሐዋሳ ከተማ ከመቀሌ 70 እንደርታ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ሐዋሳ ከተማ በሊጉ 22 ጨዋታዎችን አድርጎ በ10 ድል ሲቀናው፤ በአምስቱ ተሸንፏል። በቀሪ ሰባት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል። በጨዋታዎቹ ላይ 25 ግቦችን ሲያስቆጥር 14 ግቦች ተቆጥረውበታል። ቡድኑ በ37 ነጥብ ሦስተኛ ደረጃን ይዟል።
ተጋጣሚው መቀሌ 70 እንደርታ በሊጉ ካከናወናቸው 22 ጨዋታዎች መካከል አራቱን ሲያሸንፍ በስምንቱ ሽንፈት አስተናግዷል። በቀሪ 10 ጨዋታዎች ነጥብ ጥሏል። 15 ግቦችን ከመረብ ጋር ሲያገናኝ 24 ግቦች ተቆጥረውበታል።
መቀሌ 70 እንደርታ በ22 ነጥብ 19ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።
ሐዋሳ ከተማ ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች እንዲሁም መቀሌ 70 እንደርታ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች አላሸነፉም።
ጨዋታው ሁለቱ ቡድኖች ወደ ድል መንገድ ለመመለስ የሚያደርጉት ነው።
ሐዋሳ ከተማ ካሸነፈ ሁለተኛ ደረጃን ከነገሌ አርሲ ይረከባል። ከሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ ሁለት ዝቅ ያደርጋል።
በሌላኛው መርሐ-ግብር አዳማ ከተማ ከአርባምንጭ ከቀኑ 10 ሠዓት ላይ በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።
በውድድር ዓመቱ ካደረጋቸው 22 ጨዋታዎች መካከል ሰባቱን ያሸነፈው አዳማ ከተማ በሦስቱ ሽንፈት አስተናግዷል። በ12 ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቷል። በ22 ጨዋታዎች 20 ግቦችን ሲያስቆጥር፤ 18 ጎሎችን አስተናግዷል።
አዳማ ከተማ በ33 ነጥብ ሰባተኛ ደረጃን ይዟል።
ተጋጣሚው አርባምንጭ ከተማ በበኩሉ በ22 ጨዋታዎች ሁለቱን አሸንፎ በ10 ሽንፈት አስተናግዶ በተመሳሳይ 10 ጊዜ አቻ ወጥቷል። 14 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 27 ጎሎች ተቆጥረውበታል።
አርባምንጭ ከተማ በ16 ነጥብ የመጨረሻውን 20ኛ ደረጃ ይዟል።
አዳማ ከተማ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል። በ22ኛ ሳምንት አርባምንጭ ከተማ በኢትዮ ኤሌክትሪክ የ4 ለ 1 ሽንፈት አስተናግዷል።
ጨዋታው ሁለቱም ቡድኖች ወደ ድል መንገድ ለመመለስ የሚያደርጉት ነው።