የሊጉ መሪ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከልደታ ክፍለ ከተማ ጋር ይጫወታል - ኢዜአ አማርኛ
የሊጉ መሪ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከልደታ ክፍለ ከተማ ጋር ይጫወታል
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 1 /2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ 18ኛ ሳምንት ዛሬ ይጀመራል።
ከረፋዱ 5 ሠዓት ላይ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከልደታ ክፍለ ከተማ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ በውድድር ዓመቱ 17 ጨዋታዎችን አድርጎ 15 ጨዋታዎችን ሲያሸንፍ፤ አንድ ጊዜ ተሸንፏል። በቀሪ አንድ ጨዋታ አቻ ተለያይቷል። 39 ግቦችን ሲያስቆጥር ሰባት ጎሎች ተቆጥረውበታል።
ቡድኑ በ46 ነጥብ ሊጉን እየመራ ነው።
ተጋጣሚው ልደታ ክፍለ ከተማ በሊጉ ባደረጋቸው 17 ጨዋታዎች አራቱን ሲያሸንፍ፤ በ10 ተሸንፏል። በቀሪ ሦስት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል።
በጨዋታዎቹ ላይ 19 ግቦችን ከመረብ ሲያሳርፍ 30 ጎሎችን አስተናግዷል። ልደታ ክፍለ ከተማ በ115 ነጥብ 1ኛ ደረጃን ይዟል።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ ካሸነፈ የሊጉን መሪነት ያጠናክራል።
ልደታ ክፍለ ከተማ በ17ኛው ሳምንት ከቦሌ ክፍለ ከተማ ጋር ሁለት አቻ ተለያይቷል። ቡድኑ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታል።
በሌላኛው መርሐ-ግብር ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከቦሌ ክፍለ ከተማ ከጠዋቱ ሦስት ሠዓት ላይ በአበበ ቢቂላ መታሰቢያ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 17 ጨዋታዎችን አድርጎ 14 ጊዜ ሲያሸንፍ፤ አንድ ጊዜ ተሸንፏል። በቀሪ ሁለት ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቷል። 45 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ ሥድስት ግቦች ተቆጥረውበታል።
ቡድኑ በ44 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል።
ተጋጣሚው ቦሌ ክፍለ ከተማ በሊጉ ባካሄዳቸው 17 ጨዋታዎች ስምንቱን ሲያሸንፍ ሦስት ጊዜ ተሸንፏል። በቀሪው ሥድስት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል። 21 ግቦችን ከመረብ ጋር ሲያገናኝ 15 ግቦችን አስተናግዷል።
ቦሌ ክፍለ ከተማ በ30 ነጥብ ሥድስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በድል ጉዞ ለመቀጠል እና የዋንጫ ፉክክሩን ለማጠናከር ይጫወታል። ቦሌ ክፍለ ከተማ ወደ ድል ጉዞ ለመመለስ ይፋለማል።
ዛሬ የሚደረጉ ጨዋታዎች በዋንጫ ፉክክሩ ላይ ተጽእኖ ያላቸው ናቸው።
የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ 18ኛ ሳምንት እስከ መጋቢት 3 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል።
የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን የኢትዮ ኤሌክትሪኳ ዳግማዊት ሰለሞን በ19 ግቦች ትመራለች። ረድኤት አስረሳኸኝ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ13 ጎሎች ትከተላለች።