ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከወራጅ ቀጠና የወጣበት ወሳኝ ድል አሳክቷል

አዲስ አበባ፤ የካቲት 30/2018 (ኢዜአ)፦‎  በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 23ኛ ሳምንት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ድሬዳዋ ከተማን 2 ለ 1 አሸንፏል።

ማምሻውን በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ አዲስ ግደይ እና ናትናኤል ዳንኤል የማሸነፊያ ግቦቹን አስቆጥረዋል።

መሐመድ ኑር ናስር ለድሬዳዋ ከተማ ብቸኛውን ጎል ከመረብ ላይ አሳርፏል።

ከሁለት ተከታታይ ሽንፈቶች በኋላ ወደ አሸናፊነት የተመለሰው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ27 ነጥብ ደረጃውን ከ18ኛ ወደ 13ኛ ከፍ በማድረግ ከወራጅ ቀጠና ወጥቷል። በሊጉ ስድስተኛ ድሉን አስመዝግቧል።

በአንጻሩ በውድድር ዓመቱ ሰባተኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው ድሬዳዋ ከተማ በ28 ነጥብ 11ኛ ደረጃን ይዟል። 

በሌላኛው መርሐ-ግብር ኢትዮጵያ መድን እና ሀድያ ሆሳዕና አንድ አቻ ተለያይተዋል።

በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በተካሄደው ታሪኩ ፀደቀ በ11ኛው ደቂቃ ባስቆጠራት ጎል ሀድያ ሆሳዕና መሪ መሆን  ችሏል። 

አማኑኤል ኤርቦ በ30ኛው ደቂቃ ከመረብ ላይ ያሳረፋት ግብ ለኢትዮጵያ መድን አንድ ነጥብ አስገኝታለች።

የወቅቱ የሊጉ አሸናፊ ኢትዮጵያ መድን በ25 ነጥብ ከነበረበት 17ኛ ደረጃ ወደ 16ኛ ከፍ በማለት ከወራጅ ቀጠና ወጥቷል። 

ሀድያ ሆሳዕና በ29 ነጥብ ዘጠነኛ ደረጃን ይዟል።

ዛሬ ቀን ላይ በተደረጉ የ23ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ምድረ ገነት ሽሬ እና ፋሲል ከነማ አንድ አቻ ሲለያዩ ባህርዳር ከተማ እና ነገሌ አርሲ ያደረጉት ጨዋታ ያለ ግብ አቻ ተጠናቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም