ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የዳኝነት ሥርዓት የለውጥ እርምጃ ስኬቶች በተሞክሮነት የሚወሰዱ ናቸው

አዲስ አበባ፤ የካቲት 30/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የዳኝነት ሥርዓት የለውጥ እርምጃ ስኬቶች በተሞክሮነት የሚወሰዱ መሆናቸውን የዝምባብዌ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ሉክ ማላባ ገለጹ።

በዝምባብዌ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ሉክ ማላባ የተመራ የሀገሪቱ ልዑክ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤትን የስራ እንቅስቃሴና የለውጥ ስራዎች ጎብኝቷል።

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ቴዎድሮስ ምህረት እና የተቋሙ የስራ ኃላፊዎች በፍርድ ቤቱ አጠቃላይ የለውጥ ስራዎች ዙሪያ ለጎብኚዎቹ ገለጻና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የዝምባብዌ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ሉክ ማላባ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ የፍትህ ሥርዓት የለውጥ ስራዎች በምሳሌነት የሚጠቀሱና በተሞክሮነት የሚወሰዱ ስኬቶች ናቸው።


 

ጉብኝታቸውም ዝምባብዌ በፍርድ ቤትና የፍትሕ ሥርዓቷን ለማሻሻል በምታደርገው ጥረት ለቀጣይ ስራዎች ስንቅ የሚሆን ልምድና ተሞክሮ ማግኘታቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የዲጂታል ችሎት ሥርዓትም የዳኝነት ዘርፍ አገልግሎት አሰጣጥን ለማሳለጥ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ መሆኑን አመላክተዋል።

የፍርድ ቤቶች የዲጂታላይዜሽን የዳኝነት አሰራሮች በተቀናጀ አግባብ መመራታቸው ውጤታማ እንዲሆኑ ማስቻሉን በማንሳት፤ ዝምባብዌም ከኢትዮጵያ ልምድ ትቀስማለች ብለዋል።


 

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ቴዎድሮስ ምህረት በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በዳኝነት ሥርዓቱ ላይ ውጤታማ የለውጥ እርምጃዎችን መተግበሯን አንስተዋል።

የዝምባብዌ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ልዑካን ቡድንም የኢትዮጵያን የፍርድ ቤቶች የለውጥ ስኬቶች በልምድና ተሞክሮነት መጋራት ያስቻላቸውን ጉብኝት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

በጉብኝቱ የሀገራቱን የፍርድ ቤት ለፍርድ ቤት ግንኙነት ማጠናከር የሚያስችሉ የተሞክሮ ልውውጥ ውይይቶች መደረጋቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዲጂታል የዳኝነት ሥርዓት ቀጠሮ በማሳጠር፣ ተደራሽነትን በማስፋትና የፍትሕ ሥርዓቱን ውጤታማ በማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረጉ መሆኑን ጠቁመዋል።

በቀጣይም የዳኝነት ሥርዓቱን ውጤታማነት ለማስቀጠል ተግባራዊ የተደረጉ የለውጥ እርምጃዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም