ቀጥታ፡

የህዝብ ሰላምና አንድነት እንዲጸና አበክረን እንሰራለን - የሃይማኖት አባቶች

አርባ ምንጭ፤ የካቲት 30/2018 (ኢዜአ)፡-የህዝብ ሰላምና አንድነት እንዲጸና ለማስቻል አበክረው እንደሚሰሩ በጋሞ ዞን የሚገኙ የሃይማኖት ተቋማት አባቶች ገለጹ፡፡

"የመደመር መንግስትና ሃይማኖት ተቋማት" በሚል መሪ ሃሳብ የጋሞ ዞን የሃይማኖት አባቶች ከመንግስት አካላት ጋር በአርባ ምንጭ ከተማ ተወያይተዋል።


 

ውይይቱን በማስመልከት ኢዜአ ያነጋገራቸው የሃይማኖት አባቶች እንደገለጹት፣ የህዝብ ሰላምና አንድነት እንዲጸና በየእምነት ተቋማቸው አበክረው እንደሚሰሩ ተናግረዋል። 

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የእስልምና እምነት አባት የሆኑት ሙስጠፋ አህመድ እንዳሉት መድረኩ የሃይማኖት ተቋማት ህብረታቸውን ለማጠናከርና ችግሮችንም በውይይት ለመፍታት ጠቀሜታው የጎላ ነው።


 

መንግስትና ሃይማኖት በሀገር ሰላም፣ አንድነትና ልማት ላይ በጥምረት እንደሚሰሩ ገልጸው፣ ህዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የሰላም፣ የአንድነትና የልማት ሥራዎችን ለማስቀጠል በበለጠ እንሰራልን ብለዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አንድነት፣ ሰላምና ፍቅርን ማዕከል በማድረግ ሃይማኖታዊ ስርአቷን ስታስፈጽም መቆየቷን የተናገሩት ደግሞ የጋሞ እና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ አባ ገሪማ ጌታነህ ናቸው።

መንግስት ለሀገር ሰላም፣ ልማትና ሀገራዊ አንድነት እያደረገ ያለው ጥረት የሚደነቅ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህንኑ አጠናክሮ ለማስቀጠል የበኩላቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።

ከወንጌል አማኞች ካውንስል መሪዎች መካከል የአርባ ምንጭ ከተማ ዝግቲ በር ቃለ-ህይወት ቤተክርስቲያን የመጡት መጋቤ ማቴዎስ ኬርቤ በበኩላቸው እንዳሉት መንግስት ከሃይማኖት አባቶች ጋር በጋራ መምከሩ የሚበረታታ ነው።

የሃይማኖት ተቋማት የሰላም፣ የአብሮነት፣ የአንድነትና የዕድገት ተምሳሌት መሆናቸውን አስታውሰው፣ ተግባሩን አጠናክረን እንቀጥልለን ብለዋል። 

የሃይማኖት ተቋማት ለሌሎች የፖለቲካ ተልዕኮ ማስፈጸሚያ ሊሆኑ አይገባም ያሉት አቡነ ኤሊያስ፣ በሃይማኖት ሽፋን የህዝብን ሰላም የሚያናጉ አካላትን እናወግዛለን ብለዋል።

በሃይማኖቶች መካከል ያለው መቻቻልና መከባበር መጠናከር እንዳለበት ጠቅሰው ምዕመኑ ሰላሙንና አንድነቱን በማጽናት የፀረ-ሰላም ሃይሎችን ሴራ ማክሸፍ እንዳለበት ተናግረዋል።


 

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አበባየሁ ታደሰ (ዶ/ር)፣ የሃይማኖት ተቋማት ኢትዮጵያ ጸንታ እንድትኖር በትውልድ ግንባታ አይነተኛ ሚና አላቸው ብለዋል።

ለዘመናት የቆየው የሕዝቦች አንድነትና ትስስር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ተቋማቱ አስተዋጿቸው የጎላ መሆኑን ጠቅሰው፣ ምዕምናንን ስለአብሮነትና ሰላም በማስተማር በሰላምና ልማት ላይ የበኩላቸውን እንዲወጡ አስገንዘበዋል።

በጽንፈኝነትና በአክራሪነት የሚገለጹ ሃይሎች ለሃይማኖት እኩልነት፣ ለሰላምና ዕድገት እንቅፋት በመሆናቸው በጋራ ልንከላከላቸው ይገባል ብለዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም