ሀገራት የሴቶች መብቶችን የሚያረጋግጡ ጠንካራ እርምጃዎችን መውሰድ ይገባቸዋል- መሐሙድ አሊ ዩሱፍ - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራት የሴቶች መብቶችን የሚያረጋግጡ ጠንካራ እርምጃዎችን መውሰድ ይገባቸዋል- መሐሙድ አሊ ዩሱፍ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 30/2018 (ኢዜአ)፦ የአፍሪካ ሀገራት የሴቶች መብቶች እና የሥርዓተ ጾታ እኩልነነት የሚያረጋግጡ ጠንካራ እርምጃዎችን እንዲወስዱ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ ጥሪ አቀረቡ።
ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ለ115ኛ ጊዜ በተለያዩ ሁነቶች እየተከበረ ይገኛል።
"መብቶች፣ ፍትሕ እና የተግባር ምላሽ፤ ለሁሉም ሴቶች እና ልጃ ገረዶች" የሴቶች ቀን የሚከበርበት መሪ ሐሳብ ነው።
የአፍሪካ ኀብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ የዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን አስመልክቶ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በመልዕክታቸውም፤ ቀኑ የአፍሪካ ሴቶች እና ልጃገረድ ስኬቶችን የምናከብርበት፣ ሴቶችን ማብቃት እና ጥበቃ ላይ የገባናቸውን ቃል ኪዳኖች ዳግም የምናድስበት ነው ብለዋል።
ሴቶች በአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ከአመራር ሰጪነት እስከ ቴክኒካዊ ቦታዎች ወሳኝ ሚና እየተጫወቱ እንደሚገኙም አመልክተዋል።
የሥርዓተ ጾታ እኩልነት የተቋሙ ሥራ ማዕከል መሆኑንም አስረድተዋል።
የአፍሪካ ኅብረትም ቀኑን እያከበረ ሲሆን፤ የኮሚሽኑ ሊቀ መንበር በአፍሪካ የሴቶችን መብቶች የሚደግፉ ቁልፍ ማዕቀፎችን በዚሁ ወቅት አንስተዋል።
ለአብነትም የአፍሪካ ኅብረት የሰው እና ዜጎች መብቶች ቻርተር የሴቶች መብቶች የሕግ ማዕቀፍ፣ የሴቶች መብቶች ፕሮቶኮል (ማፑቶ ፕሮቶኮል) እና የሴቶችና ልጃገረዶች ጥቃትን ማስቆም ያለመውን የኅብረቱ ን ኮንቬንሽን በማሳያነት ጠቅሰዋል።
የኮንቬንሽኑ ወደ ትግበራ መግባት ትልቅ ስኬት እንደሆነ ገልጸው፤ ሀገራት በሕግ አውጪ ምክር ቤት ማዕቀፉን በማጽደቅ ወደ ትግበራ እንዲያስገቡ ጥሪ አቅርበዋል።
ሊቀ መንበሩ የሥርዓተ ጾታ እኩልነት እና የልማት የትኩረት መስኮች ቁርኝት እንዳለውም አመላክተዋል።
የአፍሪካ ኅብረት የ2026 ትኩረት በሆነው ውኃ እና ንጽህና ጋር በተያያዘ፤ ሀገራት የሴቶችን ጫና የሚያቃልሉ እና ተጠቃሚነታቸውን የሚያረጋግጡ ሥራዎችን እንዲያከናውኑም ጥሪ አቅርበዋል።