ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለሀገር ዕድገትና ለማኅበረሰብ ለውጥ በትጋት ሊሠሩ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለሀገር ዕድገትና ለማኅበረሰብ ለውጥ በትጋት ሊሠሩ ይገባል
አዲስ አበባ፤ የካቲት 30/2018(ኢዜአ)፦ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በተሰጣቸው ተልዕኮ መሠረት ለሀገር ዕድገትና ለማኅበረሰብ ለውጥ በትጋት ሊሠሩ እንደሚገባ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብት፣ የሥራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ነገሪ ሌንጮ(ዶ/ር) አስገነዘቡ።
ትምህርት ሚኒስቴር ለሁለት ቀናት የሚቆይ የ2018 ዓ.ም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የቁልፍ ተግባራት የግማሽ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ መድረክ በአዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብት፣ የሥራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ነገሪ ሌንጮ(ዶ/ር) በመድረኩ ባስተላለፉት መልእክት፤ ተቋማቱ የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ ብቁና ተወዳዳሪ ዜጋ ለማፍራት የጀመሩትን ተግባር አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ገልጸዋል።
በተለይም በጥናትና ምርምር እንዲሁም በማኅበረሰብ አገልግሎት ረገድ ውጤታማ ሥራዎች ሊከናወኑ እንደሚገባ ጠቅሰው ከኢንዱስትሪዎች ጋር ያለውን ትስስር በማጠናከር ተማሪዎች የተግባር ተኮር ልምምድ እንዲያገኙ መሥራት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።
ቋሚ ኮሚቴው በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የመስክ ምልከታ ማድረጉን የገለጹት ሰብሳቢው በተቋማቱ መካከል የተደረጉ የስምምነት ውጤቶች ተጨባጭ ለውጥ እያስመዘገቡ መሆኑን ጠቁመዋል።
የመውጫ ፈተና መጀመሩም ለትምህርት ጥራት መሻሻል የጎላ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ጠቁመዋል።
የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) በበኩላቸው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አሁን ካለው ተለዋዋጭ ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ ጋር ተወዳዳሪ ሆነው እንዲወጡ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አሳስበዋል።
የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ከአመራር እስከ ታችኛው የሥራ ክፍል የተቀናጀ ርብርብ እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው ተቋማቱ ለአገር ዕድገት የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ ማሳደግ እንዳለባቸውም ገልጸዋል።
የከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ኮራ ጡሹኔ እንዳሉትም ተቋማቱ በሥራ ባሕልና በቴክኖሎጂ አጠቃቀም ረገድ መሻሻል እያሳዩ ነው፡፡
በቀጣይ የትምህርት ጥራትን ከማረጋገጥ ባለፈ የምርምር ሥራዎችን ውጤታማነት ለማረጋገጥ በትጋት ይሰራል ብለዋል፡፡
የግምገማ መድረኩ ተቋማቱ ከሚኒስቴር ጋር በገቡት ውል መሠረት ያከናወኗቸውን ተግባራትና ያጋጠሟቸውን ፈተናዎች በጥልቀት በመለየት፣ በቀጣይ የተሻለ አፈጻጸም እንዲኖር ለማድረግ ያለመ መሆኑ ጠቅሰዋል፡፡