ሰላምና አንድነትን የሚያጎለብቱ ተግባራትን በማከናወን የለውጡን ትሩፋቶች ለማስቀጠል እንሰራልን - ኢዜአ አማርኛ
ሰላምና አንድነትን የሚያጎለብቱ ተግባራትን በማከናወን የለውጡን ትሩፋቶች ለማስቀጠል እንሰራልን
ሆሳዕና፤የካቲት 30/2018(ኢዜአ)፡-የህዝብን ሰላምና አንድነት የሚያጎለብቱ ተግባራትን በማከናወን የለውጡን ትሩፋቶች ለማስቀጠል እንደሚሰሩ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አባቶችና ምዕመናን ገለፁ።
"በመደመር መንግሥት እይታ የኃይማኖት ተቋማት ሚና" በሚል መሪ ሀሳብ የእምነቱ አባቶችና ምዕመናን የተሳተፉበት ክልላዊ የምክክር መድረክ በሆሳዕና ከተማ ተካሂዷል፡፡
ከማረቆ ልዩ ወረዳ ቤተ ክህነት የመጡት ቀሲስ ይትባረክ ሶዴ እንደገለፁት ሰላምና አንድነት ለሀገራዊ እድገት መሰረታዊ ጉዳይ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በመሆኑም እንደሀይማኖት አባት የህዝብን አንድነት፣ ሰላምና ልማት በሚያጎለብቱ የጋራ ጉዳዮች ላይ አተኩረው በመስራት የሀገራዊ ለውጡን ውጤት ለማስቀጠል እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡
በተለይ ትውልድን በስነ ምግባር በማነጽ ረገድ ቤተ ክርስቲያን ያላት ሚና ከፍተኛ መሆኑን ተናግረው፣ ይህን ወሳኝ ድርሻ ከመወጣት አንጻር የምታከናውናቸው ተግባራት ይጠናከራሉ ብለዋል።
የዜጎችን አብሮነትና አንድነት ለሚያጎለብቱ ሥራዎች ትኩረት መስጠት እንደሚገባ አንስተው፣ በዚህ ረገድ ተከታዮቻቸውን በማስተማር የአብሮነት እሴቶችን ከሚሸረሽሩ ሀሰተኛ መረጃዎች ለመታደግ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
"በክልሉ ያለውን ሰላም ማስቀጠል የሚቻለው በትብብር መስራት ሲቻል ነው" ያሉት ሌላኛው የውይይቱ ተሳታፊ አቶ ሙላቱ ጊቻሞ ሲሆኑ ለዚህ ደግሞ የውስጥ አንድነትና የሰላም እሴቶችን ማጠናከር ይገባል ብለዋል።
አንዱ የሀይማኖት ተቋም ለሌላው ደጀን በመሆን አብሮነታቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው ተናግረው፣ ተቻችሎና ተከባብሮ የመኖር እሴትን በማጎልበት የጋራ ተጠቃሚነትና ሰላምን ማጽናት ይገባል ብለዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሰብሳቢ ተወካይና የሀድያና ስልጤ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መላከ ህይወት ቀሲስ ንጉሴ ባወቀ በበኩላቸው፣ ከለውጡ ትሩፋቶች በዘላቂነት ተጠቃሚ መሆን የሚቻለው ሰላምን አጠናክሮ ማስቀጠል ሲቻል ነው።
ጉባኤው በሰላም ጉዳይ ከክልሉ መንግስት ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑን ተናግረው ሀይማኖትን ሽፋን በማድረግ የህዝቡን አብሮነት ለመሸርሸር የሚንቀሳቀሱ አካላትን ሁላችንም አጋልጠን ልንሰጥ ይገባል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የሀገርን ህልውና ከማስጠበቅ ጀምሮ ለሀገር መንግስት ግንባታ መጠናከር የበኩሏን አስተዋጽኦ ስታበረክት ቆይታለች ያሉት ደግሞ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) ናቸው ፡፡
ቤተክርስቲያኗ ለዘላቂ ሰላም መጠበቅና ለልማት ሥራዎች መጠናከር የራሷን አስተዋጾ እያደረገች ትገኛለች ብለዋል፡፡
ሰላምና አብሮነትን የሚያጎለብት በመልካም ሰብዕና የተገነባን ትውልድ በማፍራት ረገድ ስታከናውነው የቆየችውን ተግባር አጠናክራ ልትቀጥል ይገባል ሲሉም አስገንዝበዋል።
የህዝብን ሰላምና አብሮነት ማስጠበቅ የተጀመሩ ውጤታማ የልማትና የመልካም አስተዳደር ተግባራትን ለማጠናከር ወሳኝ መሆኑን አንስተው፣ ይህ ዕውን እንዲሆን ሁሉም የሚጠበቅበትን ሊወጣ ይገባል ብለዋል፡፡
በምክክር መድረኩ ላይ በብልጽግና ፓርቲ የክልሉ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዴላሞ ኦቶሬ (ዶ/ር) ጨምሮ ሌሎች የክልሉ አመራሮች፣ የቤተ ክርስቲያኗ አባቶችና ምዕመናን ተሳትፈዋል፡፡