ቀጥታ፡

ኢንስቲትዩቱ በምርምር የተገኙ ውጤቶችን ተደራሽ በማድረግ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሰራ ነው

ወልቂጤ፤ የካቲት 30/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በግብርናው ዘርፍ በምርምር የተገኙ ውጤቶችን ተደራሽ በማድረግ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሰራ መሆኑን ገለጸ። 

ኢንስቲትዩቱ በወልቂጤ ግብርና ምርምር ማዕከል ዝርያቸው የተሻሻሉ ጊደሮችና ኮርማዎችን ለሞዴል አርሶ አደሮችና በዘርፉ ለተሰማሩ ማህበራት የማስተላለፍ እና የመስክ ምልከታ መርሃ ግብር አካሂዷል።

በወቅቱም የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ድሪባ ገለቴ(ዶ/ር) እንዳሉት፤ ኢንስቲትዩቱ በሀገሪቱ በ23 የምርምር እና በ712 የአገልግሎት ማዕከላት አዳዲስ የምርምር ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል።


 

በሀገሪቱ አሁን ላይ ከ271 በላይ የምርምር ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ በማድረግ ምርትና ምርታማነት በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።

የግብርናውን ዘርፍ በቴክኖሎጂ በማስደገፍ የምግብ ሉዓላዊነትን ከማረጋገጥ ባለፈ የሀገሪቱን እድገት ማፋጠን የሚያስችሉ በሳይንሳዊ ምርምር የተደገፉ ዘርፈ-ብዙ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ይህም ኢንስቲትዩቱ በምርምር የተገኙ ውጤቶችን ተደራሽ በማድረግ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሰራ ለመሆኑ ማሳያ ነው ብለዋል። 

የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል እና የእንስሳት እና ዓሳ ሃብት ዘርፍ ኃላፊ ኢያሱ ተረፈ በግብርና ምርምር  የተገኘው ስኬትና ማንሰራራት ቀጣይነት እንዲኖረው የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።


 

ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ ተግባራትም ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለመሸጋገርና የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት የሚያግዙ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ባለፈው ዓመት በክልሉ የወተት ምርታማነት 675 ሚሊየን ሊትር ላይ መድረሱን ጠቁመው በዘንድሮ ዓመት 744 ሚሊየን ሊትር ለማድረስ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

ኢንስቲትዩቱ በሚያከናውናቸው የምርምር ስራዎች በዞኑ የእንስሳት ዝርያን በማሻሻል የአርሶ አደሩን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የማሳደግ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠላቸውን የገለፁት ደግሞ የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ላጫ ጋሩማ ናቸው።


 

የለውጡ መንግስት ለግብርና ልማት በሰጠው ትኩረት የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ተግባራዊ መደረጉ የእንስሳት ልማቱን በግብዓትና በአዳዲስ አሰራር ለማገዝ አስችሏል ብለዋል።

የወልቂጤ ግብርና ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር ቤተል ነክር በበኩላቸው፤ የምርምር ማዕከሉ የአካባቢውን ማህበረሰብ ችግር መፍታት የሚያስችሉ የተለያዩ የግብርና ምርምር ሥራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን ጠቅሰዋል።


 

ለዓመታት የምርምርና ብዜት ሥራ ሲከናወንባቸው የነበሩ የተሻሻሉ የኮርማ፣ የጊደርና የዶሮ ዝርያዎችን ለሞዴል አርሶ አደሮች እና በዘርፉ ለተሰማሩ ማህበራት እንዲሰጡ መደረጉንም ተናገረዋል። 

 

የሶዶ ወረዳ ነዋሪው አርሶ አደር አድማሱ ግዛው፤ ከእርሻ ሥራቸው ጎን ለጎን ዝርያቸው የተሻሻሉ የወተት ላሞቹን በማርባት ከሚያገኙት ምርት የምግብ ዋስትናቸውን ከማረጋገጥ ባለፈ ገቢያቸውን ለማሳደግ እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።


 

በምርምር ማእከሉ የተሰጧቸው ዝርያቸው የተሻሻሉ ዶሮዎች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን እንደሚያሳድግላቸው የገለፁት ደግሞ በአበሽጌ  ወረዳ የጣጤሳ ቀበሌ ነዋሪዋ ወይዘሮ መውደድ ሰርጉ ናቸው።

በወልቂጤ ከተማ ዝርያቸው የተሻሻሉ ከብቶችን በማርባት በቀን 60 ሊትር ወተት ለተጠቃሚዎች ተደራሽ እያደረጉ መሆናቸውን ያነሱት ደሳለኝ ዘበርጋ(ዶ/ር) ናቸው።


 

በዘንድሮ ዓመትም ከምርምር ማእከሉ ዝርያቸው የተሻሻሉ ጊደሮችን ማግኘታቸውን ነው የገለጹት። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም