ቀጥታ፡

በምዕራብ ወለጋ ዞን የተተገበሩ የግብርና ኢኒሼቲቮች የህብረተሰቡን የምግብ ዋስትና እያረጋገጡ ነው

ጊምቢ፤ የካቲት 30/2018 (ኢዜአ)፡-በምዕራብ ወለጋ ዞን ተግባራዊ የተደረጉ የግብርና ኢኒሼቲቮች የህብረተሰቡን የምግብ ዋስትና እያረጋገጡ መምጣታቸውን የዞኑ አስተዳዳር ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ተሊላ ተረፋ ለኢዜአ እንዳሉት በዞኑ በግብርና ዘርፍ ተግባራዊ የተደረጉ ኢኒሼቲቮች የህብረተሰቡን የምግብ ዋስትና እያረጋገጡ ናቸው።

በዞኑ ከሰላም ማሰፈን ሥራ ጎን ለጎን የህብረተሰቡን የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተሰጠው ትኩረት በተለይ በሌማት ትሩፋት መርሀ ግብር  ውጤታማ ሥራዎች እንደተከናወኑ  ገልጸዋል።

በመርሀግብሩ ተጠቃሚነት ለማሳደግም ዘንድሮ ከ116 ሺህ በላይ ዘመናዊ የንብ ቀፎ ለአርሶ አደሩ ለማሰራጨት ታቅዶ እስካሁን ድረስ 99 ሺህ 375 የንብ ቀፎ ተሰራጭቷል ብለዋል።

በንብ ማነብ ሥራው 15 ሺህ አርሶ አደሮች መሰማራታቸውንና በዓመቱ መጨረሻም 12 ሺህ ቶን የማር ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን አቶ ተሊላ ጠቁመዋል።

እንደ ዋና አስተዳዳሪው ገለጻ፣ ከንብ ማነብ ሥራ በተጨማሪ የወተት ላሞችን ዝርያ ለማሻሻል እና ለሥጋና እንቁላል ጣይ ዶሮዎች ስርጭት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው።

የሰብል ልማት ምርታማነትን ለማሳደግም የበጋ መስኖ ስንዴ ልማትን በግብርና ቴክኖሎጂ የመደገፍና የማስፋፋት ሥራ ተከናውኗል።

በዞኑ ያለውን የመስኖ አቅም በማሳደግ አርሶ አደሩን  ከዝናብ ጥገኝነት የማላቀቅና የሜካናይዜሽን እርሻ ልማትን በማስፋፋት ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑንም አቶ ተሊላ አመልክተዋል። 

በዘንድሮ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በዞኑ ከ199 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት መልማቱን ጠቁመው፣ ከዚህም 7 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ታቅዷል ብለዋል።

የስንዴ ልማቱ በኩታገጥም እየተከናወነ መሆኑን የገለጹት አቶ ተሊላ፣ ይህም አርሶ አደሮች ለሰብላቸው በጋራ ክትትልና እንክብካቤ  በማድረግ የተሻለ ምርት እንዲገኝ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ብለዋል።

ከስንዴ ልማቱ በተጨማሪ ከ20 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ ገበያ ተኮር የሆኑ አትክልቶች እየለሙ መሆኑንም አስረድተዋል።

ከአትክልት ልማቱም 3 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ ነው አቶ ተሊላ የገለጹት።

በመስኖ ልማቱ ከ134 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች እየተሳተፉ መሆኑን ገልጸው፣ በዞኑ የተተገበሩ የግብርና ኢኒሼቲቮች የህብረተሰቡን የምግብ ዋስትናና ሉአላዊነት እያረጋገጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ከልማቱ ተሳታፊ አርሶ አደሮች መካከል በዞኑ በጊ ወረዳ ነዋሪ ሱሌማን ሞሐመድ እና ኑሩ ከላሜ በማህበር ተደራጅተው በሁለት ሄክታር መሬት ላይ በሚያከናውኑት ጥምር ግብርና ተጠቃሚ ሆነዋል።

በመስኖ በዓመት ከሁለት ጊዜ በላይ አትክልቶች በማልማት ከቤት ውስጥ ፍጆታ ባለፈ ምርታቸውን ለገበያ በማቅረብ ገቢያቸውን እያሳደጉ መምጣታቸውን ተናግረዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም