ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ለማስተናገድ መመረጧ የስኬታማ የልማት ጉዞ ማሳያ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ለማስተናገድ መመረጧ የስኬታማ የልማት ጉዞ ማሳያ ነው
አዲስ አበባ፤ የካቲት 30/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናን እንድታስተናግድ መመረጧ በሁሉም መስኮች እያስመዘገበች ለምትገኘው የልማት ሥራዎች ውጤት ማሳያ መሆኑን ታዋቂ አትሌቶች ገለጹ።
ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በመጪው ሚያዚያ ወር የሚካሄድ ዓለም አቀፍ ውድድርን እንድታዘጋጅ በዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ተመርጣለች፡፡
በውድድሩ ከተለያዩ ሀገራት የተውጣጡ አትሌቶች የሚሳተፉበት ከመሆኑ ባሻገር በውድድሩ አሸናፊ የሚሆኑ አትሌቶች ከፍተኛ ሽልማት የሚያገኙበት ይሆናል።
የኢትዮጵያን መመረጥ ተከትሎ ኢዜአ ያነጋገራቸው ታዋቂ አትሌቶች እንደገለጹት፤ ይህ አጋጣሚ ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ ዕድገት አዲስ ምዕራፍ መክፈቱንና ሀገሪቱን በዓለም አቀፍ መድረክ የበለጠ ለማስተዋወቅ ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል ብለዋል።
የአጭር ርቀት አትሌቷ ፋንቱ ሚጌሶ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ውድድርን እንድታዘጋጅ መመረጧ በርካታ ጠቀሜታዎች እንዳሉት ተናግራለች፡፡
ለዚህ ስኬት ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ የልማት ስራዎች፣ በተለይም የስታዲየሞች፣ የመሮጫ ትራኮችና የከተማው መሰረተ ልማት ግንባታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ጠቁማለች።
ቀደም ሲል በሌሎች ሀገራት ስንሮጥ የምናየው ምቹ ሁኔታ፣ ዛሬ በሀገራችን እየተፈጠረ መሆኑን ገልጻ፤ ባለፉት ዓመታት በከተማ የታየው ለውጥ አስደናቂ መሆኑን ገልጻለች።
ሌላዋ የረጅም ርቀት አትሌት መሰሉ መልካሙ፣ አዲስ አበባ ውድድሩን የማዘጋጀት ዕድል ማግኘት ለአትሌቲክሱ ከሚያበረክተው አስተዋጽኦ በተጨማሪ ሀገርን ለማስተዋወቅ ትልቅ እድል እንደሚፈጥር አስታውቃለች።
መንግሥት በተለያዩ አካባቢዎች እየገነባቸው ያሉ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች የስልጠና ማዕከላት የመሮጫ ትራኮች ለአትሌቶች ምቹ ሁኔታ እየፈጠረ መሆኑን አንስታለች፡፡
ይህ ሁኔታ ለልምምድ ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረ አንስታ በአትሌቲክሱ ለሚመዘገበው ውጤት የላቀ ድርሻ እንደሚኖረውም ጨምራ ተናግራለች።
የስልጠና ቦታዎችን ይበልጥ በማስፋፋት በረጅም ርቀት የምናስመዘግበውን ውጤት በአጭር ርቀት ለመድገም በትኩረት መሥራት እንደሚገባ አትሌቶቹ በአስተያየታቸው አመልክተዋል።
ለዚህ ደግሞ ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት እየተደረጉ ያሉ ስራዎችን ማጠናከር እንደሚገባም ነው የጠቆሙት።