ቀጥታ፡

በኦሮሚያ ክልል የእንስሳት ሀብት ልማትን ለማዘመን የተቀረፁ ኢንሼቲቮች ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገቡ ነው

አዳማ፤ የካቲት 30 /2018(ኢዜአ)፦በኦሮሚያ ክልል የእንስሳት ሀብት ልማትን ለማዘመን የተቀረፁ ኢንሼቲቮች ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገቡ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለፀ።

የግብርናውን ዘርፍ እድገት ለማፋጠን አዳዲስ የምርምር ሥራዎች እየተካሄዱ ነው

በአዲስ መልክ ተከልሰው ወደ ትግበራ የገቡ  የወተት ልማት፣ ዶሮ፣ ዓሣና የእንስሳት መኖ ፓኬጆች ዙሪያ በየደረጃው ለሚገኙ የዘርፉ አመራሮችና ባለሙያዎች የተዘጋጀ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ  በአዳማ በመካሄድ ላይ ይገኛል። 


 

የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌቱ ገመቹ በዚሁ ወቅት እንደገለፁት፤ ግብርናን ለማሻገር ከተቀረፁት ኢንሼቲቮች ውስጥ የእንስሳት ሀብት ልማትን የማዘመን ስራ አንዱ ነው።

የእንስሳት ሀብቱን ውጤታማነት ለማሳደግና ዘርፉን ለማዘመን እየተተገበሩ ባሉ ኢኒሼቲቮች ተጨባጭ ውጤትና ለውጦች እየተመዘገቡ ናቸው ብለዋል።

በዚህም  የምግብ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ፣ የምግብና ስነ ምግብ ስርዓትን ለማስረፅ የሚደረገውን ጥረት የሚያሳኩ ውጤቶች እየተገኙ መሆኑን ገልፀዋል።

የእንስሳት ዝርያን ለማሻሻል የተከናወኑት ተግባራት በተለይም በሰው ስራሽ ስነ ዘዴ በማዳቀል የወተት ሀብት ልማት እንዲጨምር ከማድረግ ባለፈ የተሻሻሉ ጥጆችና ጊደሮች በስፋት እንዲወለዱ ማድረጉን ነው የገለጹት።

በየዓመቱም ከ 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ የወተት ላሞችን ማዳቀል እንደተቻለ አንስተዋል።

ልዩ ዝርያ ያላቸውን የወተት ላሞችን በመደበኛና ሰው ሰራሽ ስነ ዘዴ ማዳቀልን ጨምሮ በዶሮ ፣ ዓሣና በማር ልማት ስራ የተሻለ ውጤት መምጣቱን አንስተዋል።

የማር ልማት ኢንሼቲቭን ለማሳካት በየዓመቱ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዘመናዊ የንብ ማነቢያ ቀፎ እየተሰራጨ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የማር ምርት በዘመናዊ ቀፎ እንዲካሔድ መደረጉ ከባህላዊ ቀፎ ሲገኝ የነበረውን 10 ኪሎግራም የማይበልጥ ምርት በአማካይ 25 ኪሎግራም ለማድረስ መቻሉን ነው የተናገሩት።


 

መድረኩ የእንስሳት ሀብት ዘርፉን ለማዘመን በተሰሩ ስራዎች የተገኙ ውጤቶችና ተሞክሮዎችን አጠናክሮ በማስቀጠል ግብርናን ለማሻገር የተቀመጠውን ግብ በተቀናጀ ርብርብ ለማሳካት ያለመ ነው ያሉት ደግሞ የቢሮው የእንስሳት ሀብት ልማት ዘርፍ ሃላፊ አቶ ቶሌራ ደበላ ናቸው።

በተጨማሪም የወተት ላሞች ልማት፣ የዶሮ፣ ዓሣ፣ ማር፣ ዓሣማና የእንስሳት መኖ ልማትን ጨምሮ በአዲስ መልክ የተከለሱ ስድስት ፓኬጆች ላይ ግንዛቤ የማስጨበጥ አላማ ያነገበ ነው ብለዋል።

ይህም የእንስሳት ሀብቱን በማዘመን የምግብ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ፣ ምግብና ስነ ምግብ ስርዓትን ለማስረፅ የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት የሚያግዝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም