ቀጥታ፡

በሊጉ ነገሌ አርሲ ከባህርዳር ከተማ ፋሲል ከነማ ከምድረገነት ሽሬ የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ይጠበቃሉ 

አዲስ አበባ፤ የካቲት 30 /2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 23ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ውሎ አራት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።

ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ  ባህርዳር ከተማ ከነገሌ አርሲ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ። 

ባህርዳር ከተማ በሊጉ ባደረጋቸው 22 ጨዋታዎች በአምስቱ አሸንፎ በአምስቱ ተሸንፎ በ12ቱ አቻ ወጥቷል።  በ22ቱ ጨዋታዎች 15 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 17 ጎሎች ተቆጥረውበታል።  ቡድኑ በ27 ነጥብ 12ኛ ደረጃን ይዟል። 

ተጋጣሚው ነገሌ አርሲ በሊጉ 20 ጨዋታዎች አከናውኖ በ10ሩ ጊዜ ድል ሲቀናው በአምስቱ ተሸንፏል። ሰባት ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል። 22 ግቦችን ሲያስቆጥር 14 ጎሎችን አስተናግዷል።

አዲስ አዳጊው ነገሌ አርሲ በ37 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዟል። 

ባህርዳር ከተማ ባለፉት ሁለት የሊግ ጨዋታዎች ተሸንፏል። ተጋጣሚው ነገሌ አርሲ ባለፉት ሶስት የሊግ ጨዋታዎች ድል አልቀናውም።

ሁለቱም ቡድኖች ወደ አሸናፊነት መንገድ ለመመለስ ይጫወታሉ።

በሌላኛው መርሐ-ግብር ምድረ ገነት ሽሬ ከፋሲል ከነማ ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። 

ምድረ ገነት ሽሬ እስከ አሁን በሊጉ ያሸነፈው የጨዋታ ብዛት ስድስት ነው። ስምንት ጊዜ ሲሸነፍ በተመሳሳይ ስምንት ጊዜ አቻ ወጥቷል። 15 ግቦችን ሲያስቆጥር 16 ጎሎችን አስተናግዷል። ቡድኑ በ26 ነጥብ 14ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። 

ተጋጣሚው ፋሲል ከነማ በበኩሉ 22 ጨዋታዎችን አድርጎ ስምንት ጊዜ ሲያሸንፍ አምስት ጊዜ ተሸንፏል። በስምንት ጨዋታዎች ነጥብ ጥሏል። 16 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 14 ጎሎች ተቆጥረውበታል። 

ፋሲል ከነማ በ33 ነጥብ ሰባተኛ ደረጃን ይዟል። 

ምድረ ገነት ሽሬ በ22ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር በወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ የ1 ለ 0  ሽንፈት አስተናግዷል። 

ፋሲል ከነማ ባለፉት አምስት የሊጉ ጨዋታዎች ድል አልቀናውም። ሁለቱም ቡድኖች ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታሉ። 

ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ ኢትዮጵያ መድን ከሀዲያ ሆሳዕና በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።

የወቅቱ የሊጉ አሸናፊ ኢትዮጵያ መድን በ24 ነጥብ 17ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። ሀዲያ ሆሳዕና በ28 ነጥብ ዘጠነኛ ደረጃን ይዟል።

በ22ኛ ሳምንት ኢትዮጵያ መድን ከሸገር ከተማ፣ ሀዲያ ሆሳዕና ከአዳማ ከተማ በተመሳሳይ አንድ አቻ ተለያይተዋል። 

ሁለቱ ቡድኖች ወደ አሸናፊነት መንገድ ለመመለስ ይጫወታሉ። 

ድሬዳዋ ከተማ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያካሂዳሉ።

ድሬዳዋ ከተማ በ28 ነጥብ 10ኛ ደረጃን ይዟል። ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ24 ነጥብ 18ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።

ጨዋታው ድሬዳዋ ከተማ ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሁለት ሽንፈቶች በኋላ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ የሚያደርጉት ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም