የኤፍኤ ካፕ የጥሎ ማለፍ መርሐ-ግብር ዛሬ ይጠናቀቃል - ኢዜአ አማርኛ
የኤፍኤ ካፕ የጥሎ ማለፍ መርሐ-ግብር ዛሬ ይጠናቀቃል
አዲስ አበባ ፤ የካቲት 30/2018 (ኢዜአ)፡- የእንግሊዝ ኤፍኤ ካፕ ጥሎ ማለፍ (አምስተኛ ዙር) የመጨረሻ ጨዋታ ዛሬ በዌስትሃም ዩናይትድ እና ብሬንትፎርድ መካከል ይደረጋል።
ጨዋታው ምሽት 4 ሰዓት ከ30 ላይ በለንደን ስታዲየም ይካሄዳል።
ዌስትሃም ዩናይትድ በአራተኛው ዙር ማክስፊልድን፣ ብሬንትፎርድ በርተን አልቢዮንን በማሸነፍ ጥሎ ማለፍ ገብተዋል።
ሁለቱ ክለቦች በኤፍ ካፕ ሲገናኙ የአሁኑ ለአራተኛ ጊዜ ነው።
ከዚህ ቀደም ባደረጓቸው ሶስት ጨዋታዎች ቡድኖቹ በተመሳሳይ አንድ ጊዜ ሲያሸንፉ በቀሪው ጨዋታ አቻ ተለያይተዋል።
እ.አ.አ በ2023 ለመጨረሻ ጊዜ በውድድሩ በነበራቸው ግንኙነት ዌስትሃም ዩናይትድ 1 ለ 0 በማሸነፍ ለአራተኛ ዙር አልፏል።
ዌስትሃም ዩናይትድ ሶስት ጊዜ የኤፍኤ ካፕን ዋንጫ አንስቷል። ለመጨረሻ ጊዜ ውድድሩን ያሸነፈው እ.አ.አ በ1980 ነበር።
የብሬንትፎርድ ትልቁ የኤፍኤ ካፕ ውጤት በአራት አጋጣሚዎች ለሩብ ፍጻሜ ያለፈባቸው ናቸው።
የዛሬውን ጨዋታ የሚያሸንፈው ቡድን ሩብ ፍጻሜውን የሚቀላቀል የመጨረሻው ቡድን ይሆናል።
የ42 ዓመቱ አንድሪው ማድሌይ ጨዋታውን በዋና ዳኝነት ይመሩታል።
አርሰናል፣ ማንችስተር ሲቲ፣ ቼልሲ፣ ሊቨርፑል፣ ሊድስ ዩናይትድ፣ ሳውዝሃምፕተን እና ፖርት ቫሌ ሩብ ፍጻሜውን የተቀላቀሉ ክለቦች ናቸው።