በድሬዳዋ አዲስ የፍተሻ ላቦራቶሪ በማደራጀት አገልግሎቱ ተደራሽ ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
በድሬዳዋ አዲስ የፍተሻ ላቦራቶሪ በማደራጀት አገልግሎቱ ተደራሽ ተደርጓል
አዲስ አበባ፤ የካቲት 29/2018 (ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት አዲስ የፍተሻ ላቦራቶሪ ተደራጅቶ አገልግሎቱ ተደራሽ መደረጉን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በድሬዳዋ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት ጉብኝት አድርገዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ የትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት ድርጅቱ ዓለም አቀፍ የአሰራር ስርዓትን በመከተል ለአምራቾች፣ ለአገልግሎት ሰጪዎች፣ ለላኪዎች፣ ለአስመጪዎች፣ ለተቆጣጣሪ መስሪያ ቤቶች፣ ለምርምር ተቋማትና ለሸማቹ ማህበረሰብ የምርትና አገልግሎቶች የጥራት ማረጋገጫ አገልግሎትን እየሰጠ ነው ብለዋል፡፡
በድሬዳዋ አካባቢ ለሚገኙ አምራቾችና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ነፃ የንግድ ቀጣና እንዲሁም የደረቅ ወደብን መሰረት በማድረግ አዲስ የፍተሻ ላቦራቶሪ በማደራጀት አገልግሎቱን ተደራሽ ማድረጉን ገልፀዋል።
ተቋሙ ከዚህ ቀደም በምግብ ዘይት፣ በነዳጅ ምርት፣ በተለያዩ የምግብ ምርቶች፣ ለማስዋቢያና የዲተርጀንት ምርቶች፣ ለኮንስትራክሽን ምርቶችና ግብዓቶች የጥራት ማረጋገጫ አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡