መንግስት ለትውልድ ግንባታ ትኩረት ሰጥቷል - ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሀመድ - ኢዜአ አማርኛ
መንግስት ለትውልድ ግንባታ ትኩረት ሰጥቷል - ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሀመድ
ጅግጅጋ፤ የካቲት 29/2018 (ኢዜአ)፦ መንግስት በትውልድ ግንባታ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሀመድ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በሶማሊኛ ቋንቋ ያዘጋጀው “ኡበድሰን “ የተሰኘ መጽሄት የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሀመድ በተገኙበት በጅግጅጋ ከተማ ተመርቆ ለንባብ በቅቷል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በወቅቱ እንደገለጹት መንግስት ለትውልድ ግንባታ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል።
በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የተዘጋጀው ኡበድሰን መጽሄትም የዚሁ አካል መሆኑን ጠቁመዋል።
መጽሄቱ ለነገው ሀገር ተረካቢ ትውልድ መልካም ዜጋ ለማፍራትና የበለጸገች ኢትዮጵያ ለመገንባት ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።
መጽሄቱ የልጆችን የንባብ ብቃት የሚያዳብር ስለመሆኑ ጠቁመው፤ በተለይም ሀገራቸውን እና ባህላቸውን እንዲያውቁ በማድረግ በኩል ከፍተኛ ሚና እንዳለው አመልክተዋል።
የመጽሄቱ ለንባብ መብቃት የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በትውልድ ግንባታ ላይ እየሠራ ያለውን ሥራ አመላካች መሆኑን ጠቁመው ተግባሩን ይበልጥ አጠናክሮ እንዲቀጥል መልእክት አስተላልፈዋል።
መንግስት ብቁ ሀገር ተረካቢ ዜጋ ለማፍራት በሰጠው ትኩረት ቤተመጽሐፍትና የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን በብዛትና በጥራት እየገነባ ስለመሆኑም አንስተዋል ።
የትምህርት ጥራት በማሻሻል ብቁ የተማረ ትውልድ የመገንባት ስራ ትኩረት የተሰጠው መሆኑን ጠቁመው ተግባሩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል ።
ኡበድሰን መጽሄት ትውልድ ግንባታ ላይ ያተኮረና ለልጆች የተዘጋጀ መሆኑም ታውቋል ።